በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ- 19 ክትባት መሰጠት ጀመረ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ 19 ክትባት ዛሬ ማለትም መጋቢት 20/2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መሰጠት ጀመረ፡፡ በዚህ የመጀመሪያው ዙር የክትባት አሰጣጥ የተከተቡት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ናቸው፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ብዙ ወገኖችን እያጣን ቢሆንም ቫይረሱ ምንም የሌለ እስኪመስል ድረስ መዘናጋቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸው፣ “እኔም በዛሬው ዕለት ክትባቱን ወስጃለሁ፤ምንም የተለየ ስሜት የለውም፤ ህ/ሰቡ አልፎ አልፎ የሚወሩት አሉባልታዎች የተዛቡ መሆናቸውን አውቆ ክትባቱን በመውሰድ ራሱንና ሌሎችን ሊጠብቅ ይገባል፣” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በዚህ የመጀመሪያው ዙር 5000 ያህል ክትባቶችን ይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ለማዳረስ እቅድ የተያዘ መሆኑንና በቀጣይ ዙርም ላልደረሳቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ክትባቱን ለማዳረስ እንደሚሰራ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ የአለማችን ተመራማሪዎች የኮቪድ-19 ክትባት መገኘቱና በቅርቡም ወደ ሀገራችን መግባቱ ይታወቃል፡፡



