በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዋንጫ አቀባበል እና የእውቅና ስነ ስርዓት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዋንጫ አቀባበል እና የእውቅና ስነ ስርዓት ግንቦት 17/2013 ዓ.ም ተካሄደ
የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን 20ኛ አመት የምስረታ በአሉን አስመልክቶ ‘’ትኩረት ለትውልድ ስነ-ምግባር ግንባታ/Building an Ethical Generation/” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ፕሮግራሞች ግንቦት 16/2013 አክብሮ ውሏል፡፡ ስለሆነም በስነ-ምግባር ግንባታና በፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ ሂደት ላይ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው ተቋማት፣ ግለሰቦች እና ተማሪዎች የእውቅናና ሽልማት ስነ ስርአትም የዚህ የፕሮግራም አካል ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ከተቋማት ዩኒቨርሲቲአችን አራት ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም በስነ-ምግባር አርአያነት በዩኒቨርሲቲአችን አንጋፋ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ፤ በ9 ወር አፈፃፀም ግምገማ በተሻለ የስራ አፈጻጸም የዩኒቨርሲቲአችን ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ስጦታው አዛናው እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው የስነ ምግባር ጥያቄና መልስ ውድድር ተማሪ ወልደአረጋይ ሸርብ እና ተማሪ እየሩስ ገበየሁ ከዩኒቨርሲቲአችን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የተገኘው ሽልማት የጋራ ጥረታችን በመሆኑ ሁላችንም ልንኮራ እንደሚገባ በፕሮግራሙ ላይ የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተር ስጦታው ለመላው የዩኒቨርሲቲአችን ማህበረሰብ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ በበኩላቸው ለወደፊት ከዚህ የተሻለ ጠንክረን በመስራት ዩኒቨርሲቲአችን በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአለምአቀፍ ደረጃም ተሸላሚ እንዲሆን የበኩላችን ሀላፊነት እንድንወጣ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡




