በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የምርምር ስራዎቻቸውን ተቋቁሞ/ Dissertation Defense/ አቀረቡ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ላለፉት አራትና አምስት አመታት ገደማ በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ አራት ምሁራን የመመረቂያ የምርምር ስራዎቻቸውን በጥቅምትና ህዳር ወራት አቅርበዋል፡፡ አማካሪዎችና ፈታኞችም በአካል በመገኘትና በተለያዩ ሀገራት በመሆን በበይነ መረብ /Virtual/ የመመረቂያ ጥናት አቅራቢዎቹን ተከታትለው ለስኬት አብቅተዋል፡፡
በዚህ ሰሚስተር የመመረቂያ ጽኁፋቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ደብረወርቅ ተስገራ፣ዶ/ር ዘቢደሩ ዘውዴ፣ዶ/ር ንጉሴ ብርሀን እና ዶ/ር ታደሰ በላይነህ ሲሆኑ፣ ከነዚህም መካከል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አነስቴዥያ ትም/ክፍል መምህር የሆኑት የዶ/ር ታደሰ በላይነህ ጥናት የማህጸንና ተያያዥ አካላት ወደ ውጭ መውጣት/Pelvic Organ Prolapse/ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ይህም በተለይ እድሜአቸው ሳይደርስ በሚያገቡና ቀድመው በሚወልዱ እናቶች ላይ በብዛት የሚከሰቱ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ ለመቀነስና ብሎም ለመፍታት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የጥናቱ አቅራቢ ገልጸዋል፡፡
“እያንዳንዱ የመመረቂያ ጥናት አቅራቢ ቢያንስ አንድ ጥናት በአለም አቀፍ የምርምር መጽሄት/ / አሳትሟል፣” ያሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ካሳሁን አለሙ፣ በአጠቃላይ የጥናት አቅራቢዎቹ የምርምር ስራዎች በሀገራችን ቀዳሚ የሆኑ የጤና ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለጤና ስርዓቱና ለህብረተሰቡ ለውጥ የሚፈይዱና መፍትሄ የሚያመለክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ካሳሁን አለሙ ገለጻም የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ተቋሙ የአዲስ ሀሳብ አመንጭነት /Originality/ ፣ራስን ችሎ የመስራት/Independence / ፣መሻሻል ሊያመጣ በሚችል መልኩ በነጻነት ሀሳብን የማንጸባረቅ /Free to talk / እና የመተቸት /Critics /ሳይንሳዊ ባህልን ለማዳበር ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለ ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ “360 ዲግሪ” ብሎ የሚጠራው ከታናናሾች፣ከአቻዎች፣ከታላላቆች፣ከማህበረሰቡና ከሀይማኖት ተቋማት የመማር ፍልስፍና የጤና አጠባበቅ ተቋሙን በሀገርና በአለምአቀፍ ደረጃ ጠንካራ እንዲሆን እንዳስቻለውም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ካሳሁን አያይዘውም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በመሆን ለተመራቂዎች ስኬት የራሳቸውን አሻራ ለአሳረፉ አማካሪዎች፣ፈታኞች፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ማህበረሰብ በሙሉ ምስጋና አቅርበው ለተመራቂ ጽሁፍ አቅራቢዎቹ የእንኳን ደስ ያላችሁ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ተመራቂዎችም እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከጎናቸው በመሆን ያገዟቸውን ቤተሰቦቻቸው፣ የጥናቱ ተሳፊታዎች፣ መምህራንና ሌሎች አካላትን አመስግነዋል፡፡
**************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 22/2013 ዓ.ም







