በ2013 ዓ.ም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን እውን ለማድረግ አላማ ያደረገ ውይይት ተካሄደ
በያዝነው የትም/ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ተግባራዊ ለማድረግ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ የተማሪ አደረጃጀቶች ጋር ህዳር 26/2013 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይንን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ተባባሪ ዲኖች፣የጥበቃና ደህንነት ኃላፊዎች፣ የተማሪዎች ህብረት እና የሰላም ፎረም አባላት ተሳትፈዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን በንግግር በከፈቱት በዚህ አጭር የምክክር መድረክ፣ የያዝነው የትም/ ዘመን ሰላማዊና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ መሰረታዊ ሀሳቦች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
ስለሆነም በዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት የነበሩ መልካም ተሞክሮዎች፣ ከከተማው ማህበረሰብና ባለድርሻ አካለት ጋር ስለነበረው ትብብር በተመለከተ በአስ/ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ በአቶ ዳዊት ዳርጌ፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ማ/ሰብ ተግባራዊ ሊሆን ስለሚገባው የኮቮድ-19 መመሪያን በተመለከተ በህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የተማሪዎች ዲን በአቶ አብርሀም ታረቀኝ ሰፊ ገለጻዎች ቀርበዋል ፡፡ በተጨማሪም ከማን ምን ይጠበቃል በሚል ከሳይንስና ከፍተኛ ትም/ሚኒስቴርና ከጤና ሚ/ር የተሰጠ አቅጣጫ ላይ ትኩረት ያደረገ ማብራሪያ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት በአቶ አበባው ጌታሁን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ከተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዲን አቶ አባይ ገላነው የ2013 ዓ.ም የትም/ ዘመን ሰላማዊና ውጤታማ ይሆን ዘንድ ሁሉም የዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ ኃላፈነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
***********************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 26/2013 ዓ.ም







