ከህክምና ሳይንስና አተገባበር ጋር ተያያዥነት ያለው ስልጠና በደ/ወሎ ተሰጠ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሰቲ ከመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲና ከመካነ ሰላም ሆስፒታል ጋር በመተባበር ለ5 ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ከነሀሴ 25- 30/2010 ዓ.ም ከህክምና ሳይንስና አተገባበር ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚያከናውናቸው የመማር ማስተማር ስራዎች ፣ የአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የጥናትና ምርምር ስራዎች በተጨማሪ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ተግባራት በአቅራቢያ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉን አቀፍ ግልጋሎት ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቦታ ርቀት ሳይወሰን ለአጎራባች ዞኖችና ክልሎች በርካታ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየና አሁንም በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ልምድ ያካበቱ የዩኒቨርስቲው የህክምናና የጤና ሳይንስ ሙህራን በደቡብ ወሎ ዞን በመካነ ሰላም ከተማ ተገኝተው ለመካነ ሰላም ሆስታልና በዙሪያው ላሉ ሌሎች 4 ሆስፒታል (መርጡለ ማርያም ሆስፒታል፣ ወግዲ ሆስፒታል፣ ህዳር 11 ሆስፒታልና ሳይንት አጅባር ሆስፒታል) ላይ ለሚሰሩ የጤና ሙያተኞች ከህክምና ሳይንስና አተገባበር ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ሙህራን ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የስልጠና ዘርፎቹ አምስት ሲሆኑ እነሱም፡- ታፍነው ለተወለዱ ጨቅላ ህጻናት ሊደረግለቸው ስለሚገቡ የጤና ክብካቤ/ Basic New Born Care Resuscitation, ድንገተኛ ታካሚዎችን በማንኛውም ሁኔታ በሚገባ ማከም/Advanced Trauma Life Support (ATLS), ድንገተኛ ታካሚዎችን በፍጥነት ችግራቸውን መለየትና ማከም/Emergency Triage Assessment Treatment (ETAT), ከልብ ጋር በተያያዘ የሚሰራ ማሽን አጠቃቀም/ Electro Cardio Graph (ECG), ስለ ህክምና ጥራት/ Quality Imrovement/ ናቸው፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ወንድየ አድማሱና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታሁን በስልጠናው ወቅት ተገኝተዋል፡፡
የመቅደላ ዩኒቨርሲቲ የአንድ ዓመት እድሜ ያለው ዩኒቨርሲቲ ነው፤ በመሆኑም እንደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያሉ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች በቅርቡ ለተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ መልኩ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት የመቅደላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ወንድየ አድማሱ ናቸው፡፡ ዶ/ር ወንድየ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው አያይዘውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በብዙ ነገሮች የተሸለ መሆኑን አውስተው፣ ብዙ ኪሎሜትሮችን ተጉዘው ለመካነ ሰላምና በአቅራቢያ በሚገኙ ሆስፒታሎች ላይ ለሚሰሩ የጤና ሙያተኞች ስልጠና ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነው ለመጡ ሙህራንና ተልዕኮ ለሰጣቸው ተቋም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባባር በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡ በመሆኑም አሉ ፕ/ር መርሻ ጫኔ ይህ በመካነ ሰላም ከተማ ለጤና ሙያተኞች የሚሰጠው ከጤና ሳይንስና ትግበራ ጋር ተያያዥነት ያለው ስልጠና ከክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለሚሰሩ ስራዎች አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሙህራን በርቀት አካባቢ ለሚገኙ የሙያ አጋሮቻቸው ልምዳቸውን ለማካፈል የሚያደርጉትን ጥረት ፕሮፌሰሩ አድንቀዋል፡፡ ፕ/ር መርሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ እንደሌሎች ሁሉ ከመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በባህልና ቱሪዝም፣ እና በመሳሰሉት ዘርፎች አብሮ ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን አስመልክቶ ካነጋገርናቸው ተሳታፊዎች መካከል የመካነ ሰላም ሆስፒታል ሀኪምና የሆስፒታሉ የጥራት ማሻሻያ ኃላፊ ዶ/ር ጽጌረዳ አበራ እና የወግዲ ሆስፒታል ክሊኒካል ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሀመድ ካሳ ከስልጠናው በርካታ ሙያዊ እውቀቶችንና ልምዶችን እንዳገኙ ገልጸውልናል፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



