ከዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ ተቋማት መልካም አጋጣሚዎችና እና አስተማሪ ተሞክሮዎችን የተለመከተ አውደጥናት ተካሔደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ “Global Engagement: Opportunities and Lessons for Ethiopian Institutions” በሚል የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ መልካም አጋጣሚዎችና እና አስተማሪ ተሞክሮዎችን የተለመከተ አውደጥናት ግንቦት 11/2015 ዓ.ም በአሉምኒየም አዳራሽ ተካሔደ።
አለምአቀፋዊ ተሳትፎ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያስፈልግበትን ምክንያት እና ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች በተመለከተ በአውደጥናቱ ላይ ተገኝቸው ገለፃ ያደረጉት የቀድሞው የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የአሁኑ የኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ የአለምአቀፍ ምርምርና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተሾመ ይዘንጋው፣ ተቋማት በአለም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን በትብብር መስራት እንደሚያስፈልጋቸው አብራርተዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወዳዳሪ ስታፍ ፣ ውጤታማ ምርምር እና ጥራት ያለው የትምህርት አሰጣጥ እንዲኖራቸው አለምአቀፋዊ ተሳትፏቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተለያዩ የአለም ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ እንደ ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ወረርሽኝና የመሳሰሉትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አለምአቀፍ የተሳትፎ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋልም ተብሏል።
የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ስለሚያደርጉት አለምአቀፋዊ ተሳትፎ ለአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮዎቻቸውን ሊያካፍሉ እንደሚገባም ዶ/ር ተሾመ ገልፀዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው በተለያዩ ሀገራት ኃላፊነትን ተቀብለው በመስራትና በትምህርት ያካበቱትን ልምድ በአውደጥናቱ ተገኝተው ያካፈሉትን ዶ/ር ተሾመ ይዘንጋውን አመስግነዋል።
ገለፃውን ተከትሎም ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በዚህም መሰረት
ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ የመንግስት ድጋፍ ስለሚቀንስ ሊከሰቱ የሚችሉትን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም በትብብር መስራት የተሻለ ሊሆን ይገባል ተብሏል።
በአለምአቀፍ ትስስር ሒደት የምሁራን ፍልሰት ሊያጋጥም የሚችል ችግር መሆኑም ተነስቷል፤ ስለሆነም የምሁራን ፍልሰታቸው አነስተኛ ከሆኑ ተቋማት ልምድ መቅሰም እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ለተሻለ የተቋማት ተሳትፎ መኖር ብቃት ያለው የትምህርት ተቋማት መሪ ወሳኝ መሆኑም ተነስቷል።
በአውደጥናቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።