
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጦሮታ ለተሰናበቱ ሰራተኞች የምስጋና ፕሮግራም ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለረዥም አመታት በተለያዩ የስራ ክፍሎች አገልግለው በእድሜ ብቁነት በጦሮታ ለተሰናበቱ ሰራተኞች ግንቦት 26/2013ዓ/ም በኦሎምፒክ ሆቴል አዳራሽ የምስጋና መርሀ ግብር አካሄደ፡፡
በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር ጋሻው አንዳርጌ፣ የሰው ሀብት አስተዳደር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ዳርጌ፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ 220 የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው የክብር እንግዶችና፤ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ መጀመሪያ የጎንደር የዩኒቨርሲቲ የሰው ሀብት አስተዳደር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ዳርጌ ስለ ዕለቱ ፕሮግራም አጭር መግለጫ ያቀረቡ ሲሆን በጦሮታ ለተሰናበቱ ሰራተኞችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲውን የሰው ሀይል ዙሪያ ሰፊ ገለፃ አቅርበዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው በጦሮታ የተሰናበቱ ሰራተኞች ዩኒቨርሲቲውን ለረዥም አመታት በማገልገል ከሀገራችን ምርጥ ከሚባሉ፣ በአለማችንም አንቱ ከሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲካተት ያደረጉ የረዥም አመታት አገልጋይ ሰራተኞች በመሆናቸው ሊኮሩ እንደሚገባቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግራቸው ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አስራት አያይዘውም በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው እንደ ትልቅ ስኬት የሚያዩት ዩኒቨርሲቲውንና ማህበረሰቡን ለረዥም ጊዜ ያገለገሉና የመሩ፣ ተቋሙን አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያበቁ ሰዎችን ክብር ተሰጥቷቸው ማየታቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየሰሩ ለሚገኙ ሰራተኞችም ትልቅ አደራ እንደሆነ ያላቸውን አምነት ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በጦሮታ ለተሰናበቱ የዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ብቻ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነፃ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና መድህን እንዲሸፈንላቸው መወሰኑን ዶ/ር አስራት አብስረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአብራካቸው ለተፈጠሩ ልጆቻቸው በዩኒቨርሲቲው እንዲማሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ግንቦት 26 ቀን ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጦረተኞች ቀን ሆኖ እንዲታሰብ ተወስኗል፣ በዩኒቨርሲቲውና በእነርሱ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ አምስት አባላት ያሉት ማህበር ተቋቁሟል፣ በየዓመቱ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን በሚያስመርቅበት ወቅት እንዲገኙም ተጋብዘዋል፡፡

በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር ጋሻው አንዳርጌ ተቋሙ ለደረሰበት ደረጃ በተለያዬ መንገድ የላቀ አስተዋፅዖ ያበረከቱ በጦሮታ የተሰናበቱ ሰራተኞችን አመስግነው፣የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ገፅታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ የጎንደር ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ፋብሪካ፣ የሰላም ምልክት ተምሳሌታዊና አርአያ የሚሆን ተቋም ነው የሚሉት ፕ/ር ጋሻው ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተበት ከ1947ዓ/ም ጀምሮ ያለውን ሁለንተናዊ እድገት አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በጦሮታ የተሰናበቱ ሰራተኞች ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተው በድጋሜ ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት ገልጸዋል፡፡ የቀረበውን ፅሁፍ መነሻ በማድረግና በዕለቱ ፕሮግራም ዙሪያ አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመጨረሻም ከዩኒቨርሲቲው በጦሮታ ለተሰናበቱ ሰራተኞች የምስክር ወረቀት በመስጠት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡




