ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ታሳቢ ያደረገ በዓል ተከበረ
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ለ45ኛ ጊዜ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲያችን ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንን (march 8) “የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች መጋቢት 30/2013 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ አንባ አዳራሽ ተከብሮ ውሏል፡፡

የሴቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ መከበሩ ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭቆና፣ ብዝበዛና አድሎ እንዲሁም ሌሎች ፆታዊ ትንኮሳን በተመለከተ የሚደርስባቸውን ጫና በጋራ ለመታገል በአንድ ላይ ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ቀንን ታሳቢ ለማድረግ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኝ በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር የተጀመረው በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ቢሆንም በሃገራችንም የበአሉ መከበር የሴቶችን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውንና ተሳትፎአቸውን ትኩረት ለመስጠት ትርጉም እንደሚኖረውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ስመኝሽ ቸኮል በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ዕለቱን በተመለከተ የመወያያ ፅሁፍ በአቶ አለሜነህ ጌታነህ (የስርዐተ- ጾታና አድገት ት/ት ክፍል መምህር) ቀርቧል፤ጽሁፉን ተከትሎም ውይይት ተካሂዷል፡፡ እንዲሁም ዶ/ር ክቡር ይሁኔ (የባዮኬሚስትሪ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ) የህይወት ተሞክሮአቸውን አካፍለዋል፡፡
በአቶ እንግዳው መወሻ(የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ባልደረባ) አዝናኝና አስተማሪ መጣጥፍ በታጀበው በዚህ በዓል፣ለሴት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት እና በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይና የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት በዶ/ር ካሳሁን ተገኘ እና በቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት በዶ/ር መሰረት ካሴ በኩል ተበርክቶላቸዋል፡፡





