ዜና እረፍት
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት ሲያገግሉ የነበሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር አንዳርጋቸዉ ጥሩነህ በደረሰባቸዉ አደጋ በህክምና ሲረዱ ቆይተዉ ግንቦት 7/2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ዶ/ር አንዳርጋቸዉ ጥሩነህ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤት በህግ ማስተማር፤ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ደከመኝ ሳይሉ ሲያገለግሉ የቆዩ አንቱ የተባሉ ምሁር ነበሩ፡፡ ዶ/ር አንዳርጋቸዉ ጥሩነህ ለሀገርና ትዉልድ ታላቅ ጠቀሜታ ያላቸዉ መፅሃፍትን በማሳተም ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ምሁር ሲሆኑ ለምሳሌ ያክል በበርካቶች ተፈላጊና ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆነዉን “የኢትዮጵያ አብዮት እ.ኤ.አ ከ1974-1987” ጨምሮ ፤የሚዲያ ህግ በኢትዮጵያ እና የአካል ጉዳተኞች ህግጋትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የምርምር ስራዎቻቸዉን በመፅሃፍት መልክ አሳትመዋል፡፡ ዶ/ር አንዳርጋቸዉ ከእነዚህ ታዋቂ ስራዎቻቸዉ በተጨማሪ ለዘላቂ ልማትና አካባቢያቸዉ ባላቸዉ ቀናኢነት ምክኒያት በጎርጎራ አካባቢ የደንና አካባቢ ልማት ላይ በመሳተፍና ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ የነበሩ ሃገር ወዳድ ታላቅ ምሁር ነበሩ፡፡ ዶ/ር አንዳርጋቸዉ ከወጣትነታቸዉ እስከ እለተሞታቸዉ ድረስ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትና እነዚህን በመሰሉ ስራዎች በኃላፊነት ጭምር በትጋት ማህበረሰባቸዉን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ምንም እንኳን በእንግሊዝ ሃገር ረጅም ጊዜን ቢያሳልፉም ያካበቱትን እዉቀትና ልምድ ለህዝባቸዉ ጥቅም ለማዋል በማሰብ የተመቻቸ ኑሯቸዉን ጥለዉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ት/ቤትን በመቀላቀል በመጀመሪያ ዲግሪና ሁለተኛ ዲግሪ የህግ ምሩቃንን በማስተማርና በማማከር በርካታ የእዉቀት ልጆችን ያፈሩ ምሁር ነበሩ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አመራርና ማህበረሰብ እና የህግ ት/ቤት የስራ ባልደረቦቹ በዶ/ር አንዳርጋቸዉ ጥሩነህ ህልፈተ-ህይወት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ቀብራቸዉ ግንቦት 8/2012 ዓ.ም ጠዋት በቅዱስ ጭርቆስ ቤተክርስቲያን የሚፈፀም መሆኑን እየገለጽን ለቤተሰቦቹ መጽናናትን እንመኛለን፡፡



