የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ቅድመ-ምረቃ ተማሪወችን እርካታ ለመዳሰስ የተሰራ የጥናት ውጤት አለምአቀፍ የሴቶች ቀን በኮሌጁ ታስቦ በዋለበት ቀን ቀረበ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ሚድዋይፈሪ ት/ቤት ከኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ጋር በመተባበር የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ቅድመ-ምረቃ ተማሪወች እርካታን ለመዳሰስ የሰራውን የጥናት ውጤት አለምአቀፍ የሴቶች ቀን በኮሌጁ ታስቦ በዋለበት ቀን ሚያዚያ 9/2013 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ አቀረበ፡፡ በፕሮግራሙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው፣ በጤና ሚኒስቴር የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም እና የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካሌን ጨምሮ የተለያዩ የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጁና አጠ/ስ/ሆስፒታሉ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የሚድዋይፈሪ ት/ቤት ከኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ጋር በመተባባር በስነ ተዋልዶ ጤናና ተያያዥ ጉዳዮች ፈርጀ ብዙ ሰራዎችን እየሰራ መሆኑን የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ዋና አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ ላለፉት መቶ አመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና መብት ለማስከበር በተደረጉ ጥረቶች ብዙ ለውጦች ቢኖሩም ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ግን ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅና አጠ/ስ/ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከኮቪድ-19 በላይ የእናቶች ሞት በጣም ያሳስባል፤ስለሆነም በእናቶች ሁለንተናዊ ህይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ተማሪዎችን ማብቃት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካሌ በቁልፍ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡


ቁልፍ ንግገሩን ተከትሎም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚድዋይፈሪ ት/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረቱ ሞላ እና የክሊኒካል ሚድዋይፈሪ ባልደረባ በሆኑት አ/ፕሮፌሰር ባየ ከልካይ አመካኝነት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም ሪፖርት እና የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ ቅድመ-ምረቃ ተማሪወችን እርካታ ለመዳሰስ የተሰራው የጥናት ውጤት ለታዳሚዎች ቀርቦ አጠቃላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ የእርካታ ጥናቱ በመማር ማስታማር፣ በአስተዳደርና በስነ ተዋልዶና ጤና ተደራሽት የተማሪዎችን እርካታ ለመዳሰስና አስፈላጊውን ማሻሻያ ለማድረግ አላማ አድረጎ መሰራቱን አቶ ምህረቱ ሞላ አብራርተዋል፡፡

በእለቱ ታሳቢ ሆኖ የዋለውን አለምአቀፍ የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግም በትምህርት አፈጻጸማቸው ብልጫ ላሳዩ ለአስራ ሁለት ሴት ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡



