የመምህራንና የተማሪዎች የጋራ ጉባኤ ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ጥር 14/2012 ዓ/ም የመምህራንና የተማሪዎች የጋራ ጉባኤ በማራኪ ግቢ አልሙኒዬም አዳራሽ አካሄደ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የኮሌጁ ዲን ወ/ሮ መሰረት ሀሰን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ አቶ ሳሙኤል አስናቀ የዩኔስኮ ተወካይ፣ የዩኒቨርሲቲው መምህር የሆኑት ዶ/ር ክቡር ሁኔ፣ ዲኖች፣ መምህራን፣ተማሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት ጉባኤው ተካሂዷል፡፡

በጉባኤው የዩኔስኮ ተወካይ የሆኑት አቶ ሳሙኤል አስናቀ ትምህርትና ሰላም በሚል ለውይይት መነሻ የሚሆን አብይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲያችን መምህር ዶ/ር ክቡር ሁኔ የህይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉ ሲሆን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ አባንግ ሜቶ ደግሞ ብዝሀነትና አንድነት በሚል አነቃቂ ንግግር አድርገዋል፡፡ በጉባኤው የቀረቡ ሀሳቦችን መነሻ በማድረግ በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመጨረሻም በኮሌጁ የላቀ አፈፃፀም ለነበራቸው መምህራን በተማሪዎች ሽልማት ተበርክቷል፡፡ ፕሮግራሙ በዩኒቨርሲቲው የኪነ-ጥበብና ባህል ማዕከል ሙዚቃና ግጥም የደመቀ ነበር፡፡



