“የመምህራን አቅም መጎልበት ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ቁልፍ ሚና አለው!”
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ትምህርት ኮሌጅ የትምህርት ቤት መሻሻልና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለመምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት 2ኛ ደ/ት/ቤት ከየካቲት13-14/2012 ዓ.ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ዲን ተወካይ ዶ/ር ማርቆስ ተዘራን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው እና የጎንደር ዙሪያ ወረዳ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት ስልጠናው ተጀምሯል፡፡
ስልጠናው የተሰጠው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ታስቦ እንደሆነ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ዲን ተወካይ ዶ/ር ማርቆስ ተዘራ ገልጸዋል፡፡ጥራት ያለው ትምህርት የሚኖረው በዋናነት በመምህራን ብቃት ነው ፤ ስለሆነም ይህ ስልጠና መሰጠቱ “በክህሎት፣በእውቀቀትና በአመለካከት ብቃት ያላቸው መምህራንና የትምህርት አመራሮች ለማፍራት ያግዛል ፤ ጥራት የበርካታ ሁኔታዎች መስተጋብር ውጤት ቢሆንም የመምህራን አቅም መጎልበት ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ቁልፍ ሚና አለው፣” ሲሉም ዶ/ር ማርቆስ አብራርተዋል፡፡ በስልጠናው የትምህረት ባለሙያዎች መካተታቸውም ቴከኒካዌ ክህሎት እንዲኖራቸውና መምህሩን በአግባቡ ማገዝ እንዲችሉ ለመርዳት እንደሆነም ዶ/ር ማርቆስ አክለዋል ፡፡
ስልጠናው የተሰጠው በረ/ፕሮፌሰር መንበር እንየው፣በአቶ ሀብታሙ ረታ እና በአቶ ሙሉቀን አያሌው ሲሆን ዋና ትኩረትም በትምህርት ቤት መሻሻል ፣በተግባር ተኮር ምርምር እና በአሳታፊ የመማር ማስተማር ዘዴ ላይ ነው፡፡ ሰልጠናው መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ያላቸውን ግንዛቤ በማስፋት የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳለው አንዳንድ የስልጠናው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የትምህርት መሻሻል ዕቅድ አዘገጃጀት ላይ ትክክለኛ የት/ቤት ፍላጎት ለይቶ ያለማቀድ፣ የቆዩ እቅዶችን የመድገም፣ እቅዶቹን በልማዳዊ መንገድ የመተግበር ችግሮች ከዚህ በፊት እንደሚስተዋሉ የማክሰኝት አጠ/ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ጉድኝት ሱፐርቫይዘር እሸቱ ገበየሁ አንስተዋል፡፡ ስለሆነም ይህ ስልጠና መሰጠቱ ከስትራቴጅካዊ እቅድ ሂደትና አተገባባር ጋር የተያያያዙ የግንዛቤ ክፍተቶችን ይሞላል ብለዋል፡፡ ስልጠናው ስለተግባር ተኮር ምርምር አሰራር ሰፊ ግንዛቤ ከመፍጠሩም በላይ የችግሩ ባለቤት መምህራን ከስራቸው ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት በራሳቸው መፍትሄ እንዲሰጡ እንደሚያበረታታም ሱፐርቫይዘሩ አያይዘውም ገልጸዋል ፡፡አሳታፊ የመማር ማስተማር ሂደትን በተመለከተም በአብዛኛው ከፍሎች የሚማረው ተማሪ ቁጥር ከፍተኛ ስለሆነ እንዲህ አይነቱን ክፍል እንዴት በአሳታፊ የማስተማር ዘዴ ማስተማር እንደሚቻልም ጥሩ ግንዜቤ ፈጥሯልም ብለዋል፡፡
“የትምህርት ስራ የሚሰራው በቅንጅት ነው፡፡ ትልቁ ክፍተት የት/ቤቶች ስትራቴጅካዊ እቅድ በሚታቀድበት ጊዜ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሳይሆን በተወሰኑ ኮሚቴዎች ብቻ ነው፣” ያሉት ሰልጣኝ ደግሞ መ/ር ሰለሞን ብርሃኑ ናቸው ፡፡ ስለሆነም የእቅድ ትግበራው ብዙ ጊዜ ውጤታማ ሳይሆን እንደሚቀርም ገልጸዋል፡፡ በርካታ ችግሮች በየት/ቤቱ ቢኖሩም በምርምር እነዚህን ችግሮች መፍታቱ ላይ አብዛኛው መምህር በትኩረት እየሰራ እንዳሆነ የተናገሩት መ/ር ሰለሞን ፣ ስልጠናው በተክክል ስለማቀድና መተግበር ፣ተግባራዊ ምርምሮችን ስለማድረግና ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ስለመፍታት ትልቅ አቅም ስለሚፈጥር ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡፡፡ የመምህሩንና የትምህርት ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት እየተሰጠ ያለው ስልጠና በጣም የሚደነቅ ነውና በሌሎች አካባቢዎችም ስልጠናው ቢሰጥ መልካም ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል መ/ር ሸጋው ታረቀኝም የመ/ር ሰለሞንን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ በተለይ ይላሉ መ/ር ሸጋው ፣” እቅድ ሲታቀድ የትምህርት ቤቱን መሰረታዊ ችግሮች መሰረት አድርጎ ተማሪውን ፣ ህብረተሰቡን፣ መምህሩንና ሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ማሳታፍ እንደሚያስፈልግ ስልጠናው በቂ ግንዛቤ ይፈጥራል ፡፡” ስልጠናው በቂ እውቀት፣ ክህሎትና ሰፊ ልምድ ባላቸው እንደነ ረ/ፕሮፌሰር መንበር እንየው በመሰሉ አሰልጣኞች በመሰጠቱ መምህራን ስለተግባራዊ ምርምር ፣ አሳታፊ የማስተማር ሂደትና ስትራቴጅካዊ እቅድ ያላቸውን ግንዛቤ እንደሚያሰፋም መ/ር ሸጋው ገልጸዋል፡፡
አለም ሁልጊዜ በለውጥ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ከለውጡ ጋር አብሮ መሄድ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በተለይም መምህራን ትውልድን የሚያሻጋግሩ ድልድዮች እንደመሆናቸው መጠን ከዘመኑ አሰራር ጋር አብሮ ለመሄድ የእውቀት፣ ክህሎትና ግንዛቤ አድማሳቸውን በሰራ ላይ ስልጠና ማስፋታቸው ለትምህረት ጥራት መጠበቅ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



