የመስኖ ሀብት ልማትን ማሳደግ የሚችል የሶፍትዌር (software) ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ምሁራን በምዕራብና በምስራቅ በለሳ ወረዳዎች ለሚገኙ በመስኖና ተዛማች ስራዎች ለተሰማሩ ባለሙዎች የመስኖ ሀብት ልማትን ማሳደግ የሚያስችል የሶፍት ዌር (software) ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በአርባያና በጉኃላ ከተሞች የተሰጠው ይህ ስልጠና ከጥቅምት 23 እስከ ጥቅምት 29/2013 ዓ.ም ቆይታ የነበረው ሲሆን 60 የግብርና ሙያተኞችን ተሳታፊ ያደረገ ነበር፡፡
ክሮፕዋት (CROPWAT) – የመስኖ ውሀን በተመጣጠነ ሁኔታ መጠቀም የሚያስችል ሶፍት ዌር፣ ጂ.አይ.ኤስ(GIS) – በመስኖ የለሙና መልማት ያልቻሉ ቦታዎችን ለመለየት የሚያግዝ ሶፍትዌር እና ጎግል ኧርዝ (Google earth) – በመስኖ ውሀ የሚለማው ቦታ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ እሚረዳ ሶፍት ዌር ለሙያተኞች ማስተዋወቅና አጠቃቀማቸውን ማሳየት የስልጠናው ዋና ተልዕኮ ነው፡፡ የውሀ ብክነትን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ደግሞ የስልጠናው ዋና አላማ ነው፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር፣ የማ/ሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሀም ባይህ ቦታው ድርስ በመገኘት ስልጠናውን በንግግር ከፍተዋል፡፡ የስራ ባልደረቦቻቸው ያላቸውን እውቀት ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ማጋራት በመቻላቸው በዶ/ር አብርሀም በኩል ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡
ይህ ስልጠና ለግብርና ሙያተኞች አዲስና በአይነቱ ለየት ያለ የቴክኖሎጂ ስልጠና መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሀይድሮሊክስ መምህርና ተመራማሪ አቶ ዳንኤል ገለታው ገልጸዋል፡፡ ተመሳሳይ ስልጠና በሌሎች አካባቢ ለሚገኙ ሙያተኞች እንደሚሰጥ አስተባባሪው አያይዘው ገልጸዋል፡፡
**********************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም







