የሙዚቃ ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪ ስርአተ ትምህርት ግምገማ ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የሙዚቃ ጥበባት ትምህርት ክፍል የሙዚቃ የሁለተኛ ዲግሪ ስርአተ ትምህርት ግምገማ (Curriculum Review Validation Work Shop MA in Music) አውደ ጥናት ሰኔ 24/2013ዓ/ም በማራኪ አልሙኒየም ህንፃ አካሄደ፡፡
በመርሐ ግብሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ፣ የኮሌጁ ም/ዲን ዶ/ር አእምሮ አስማማው፣ ከአዲስ አበባ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ወ/ሪት ሰላማዊት ተስፋና አቶ ታደለ ጥላሁን፣ የኮሌጁ መምህራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኮሌጁ ም/ዲን ዶ/ር አእምሮ አስማማው ፕሮግራሙን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያስጀመሩ ሲሆን በዚህ በሙዚቃ የሁለተኛ ዲግሪ ስርአተ ትምህርት ግምገማ አውደ ጥናት ላይ የተገኙ አካላትን አመስግነዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 87 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞችን ፣ 134 የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን እየሰጠ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ንግግራቸው ያወሱት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ኮሌጁ በኪነጥበብ ዘርፍ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን አያይዘው ይህንን የሙያ ዘርፍ ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲው የሙዚቃ የማስተርስ ፕሮግራም መክፈቱ ያለውን አስተዋዕፆ በመግለፅ በዕለቱ የተገኙ አካላትን አመስግነዋል፡፡

በመቀጠል በኮሌጁ ረዳት ሬጅስትራር ሀላፊ በመ/ር ብስራት ወርቁ ስርአተ ትምህርቱን ለመቅረፅ በተሰራው የፍላጎት ዳሰሳ ዙሪያ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የፊልምና ቴሌቪዥን ትምህርት ክፍል መምህር በሆኑት በመ/ር ምስጋናው አለሙ ደግሞ የስርአተ ትምህርቱ ረቂቅ የቀረበ ሲሆን ጽሁፉን መነሻ በማድረግ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኋላ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡





