የማህበረሰብ ውይይት በእንፍራዝ ከተማ ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከጉዛራ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ጋር በመተባበር “ትምህርታዊ ድግስ ወትይእንታዊ ንግስ” በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 9 – 12 የቆየ የማህበረሰብ ውይይት በእንፍራዝ ከተማ በጉዛራ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ ቤት አካሂዷል፡፡
እውቁ የሙዚቃ ባለሙያና ተመራማሪ አርቲስት ሰርፀ ፍሬ ስብሀት፣ ደራሲና የቲያትር ባለሙያው አርቲስት አንዱአለም አባተ(የአጸደ ልጅ)፣ ኮሜዲ ምትኩ ፈንቴ(ሀኪም አድነው)፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዩኒቨርስቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን መስፍን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በውይይቱ ተሳትፈዋል፡፡
[widgetkit id=9206]
የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለይም ደግሞ ወጣቱን ከተለያዩ ደባል ሱሶች በዋናነት ከጫት እንዲርቅ ማድረግና በአካባቢው የሚገኘውን ታሪካዊና ጥንታዊውን የጉዛራ ቤተ-መንግስትን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ብሎም የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የውይይቱ ዋና ዋና ዓለማዎች መሆናቸውን የውይይቱን ሐሳብ ካመነጩት ከመ/ር አራጋው ገበየሁ አንደበት ከቦታው በመገኘት ለማወቅ ችለናል፡፡
አቶ ሰሎሞን መስፍን እንኳን በደህና መጣችሁ በማለት በእንፍራዝ ከተማና በአካባቢው፣ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውንና ለወደፊት በተቋሙ የታሰቡ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችን በሪፖርት መልክ በማቅርብ ውይይቱን ከፍተዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘውም የአካባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ ሊለውጥ የሚችልና በአካባቢው የሚገኘውን (ከጎንደሩ አጼ ፋሲለደስ ግንብ/ዓብያተ መንግስታት በፊት በአጼ ሰርጸ ድንግል የተገነባውን) የጉዛራ ቤተ መንግስትን ይበልጥ ሊያስተዋውቅ የሚችል ፕሮጀክት ከአለና ወደ ዩኒቨርሲቲው ጎራ ካለ፣ ዩኒቨርሲቲው አብሮ ለመስራት ሙሉ ፈቃደኝነት እንዳለው አበክረው ገልጸዋል፡፡
የጉዛራ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የታሪክ መምህር የሆኑት መ/ር አራጋው ገበየሁና የጅኦግራፊ መ/ር የሆኑት ወንድምአገኝ ጌጡ ለውይይት መነሻ የሚሆን ከጫት ጋር የተያያዘ ጥናታዊ ጹሁፎችን አቅርበዋል፡፡ ውይይቱን የመራው አርቲስት አንዷለም አባተ ሲሆን፣ የቀረበውን ጥናታዊ ፅሁፍ መነሻ በማድረግም ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
አርቲስት ሰርፀ ፍሬስብሃትና አንዱአለም አባተ ወጣቱ ከጫት እንዲርቅ የሚያስችል ወንድማዊና አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ አርቲስቶቹ ሙያዊ ድጋፍ ለሚሻ ለአካባቢዊ ማህበረሰብ በሙሉ አቅም በፈቀደ መልኩ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡
ሌሎች ተሳታፊዎችም የአካባቢው ወጣት ጊዜውን አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፍ ለማድረግ ለተለያዩ የመዝናኛ ማዕከላትና ለቤተ-መጻህፍት ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡
በሙዚቃ፣ በቀልድ(በሀኪም አድነው)፣ በእግር ኳስ ውድድር፣ በሩጫ ውድደር፣ በጉዞና በተለያዩ አውደ ርዕይዎች በእንፍራዝ ከተማ የተካሄደው ዝግጅት በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡
ወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል ከደባል ሱሶች ራሱን በማራቅ ሀገር ተረካቢና አምራች ዜጋ እንዲሆን ለማስቻል፣ በስራቸው ውጤታማና ተወዳጅ፣ በስነ-ምግባራቸው ደግሞ ምስጉን የሆኑ ታላላቅ ሰዎችን በአካል በመጋበዝ የሚደረግ ውይይት፣ ታዳጊዎች የታዋቂ ግለሶቦችን ውጤታማነት በመረዳትና አርዓያ በማድረግ በመልካም ስነ-ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ ለማድረግ ድርሻው የጎላ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም መሰል ውይይቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታችን ነው፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



