የማህፀንና ፅንስ ህክምና ት/ክፍል ስለማህፀንና ተያያዥ አካላት መላላት ቀዶ ህክምና ሀገር አቀፍ ስልጠና ሰጠ
እናቶች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከማህጸንና ጽንስ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊያጋጠማቸው ይችላል፡፡ የችግሮቹን መነሻና ህክምናውን በውል ካለወማቅም የተነሳ በተለይ በገጠሩ አካባቢ ያሉ ወላዶች ሽንትና ሰገራ መቆጣጠር አለመቻልና የማህጸን መውረድ ሲያጋጥማቸው ራሳቸውን ከማህበራዊ እንቅስቃሴ በማግለል አንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ከማህፀንና ፅንስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከልና ደረጃውን የጠበቀ ህክምና ለመስጠት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናና ከፍተኛ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም መንግስቱ ይገልጻሉ፡፡

ይህንን የጤና ችግር ታሳቢ በማድረግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ት/ክፍል በጀርመን ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ምሁራን (ዶ/ር ደብሩ ጉባና ዶ/ር አና ኬፈር) ጋር በመተባበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለመጡ የማህፀንና ፅንስ ሀኪሞች የማህጸን ድጋፍ መላላትና ተያያዥ ችግሮች ቀዶ ህክምና የተመለከተ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መጋቢት2 ና 3/2013 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ስልጠናው የሀኪሞችን የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ክህሎት ለማዳበር ታስቦ የተሰጠ መሆኑን ዶ/ር ዘላለም መንግስቱ ገልጸው፣ ለስልጠናው አስፈላጊውን የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትን ዶ/ር ደብሩ ጉባ እና ዶ/ር አና ኬፈርን አመስግነዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያዎቹ የህክምና ተመራቂ ምሁራን አንዱ የሆኑትና በሀገረ ጀርመን የሚኖሩት ዶ/ር ደብሩ ጉባ በበኩላቸው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ራሱን ችሎ የማህጸን ድጋፍ መላላትና ተያያዥ ችግሮችን የተመለከተ ሀገር አቀፍ ስልጠና መሰጠቱ ትልቅ ደስታና ተስፋ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ አውደጥናቱ የበለጠ መስፋፋት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የማህጸንና ተያያዥ አካላት ችግሮች ላይ ደረጃውን የጠበቀ ህክምና በመስጠት የእናቶችን ችግር ለማሻሻል እና የህክምና ክህሎትን በማዳበር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህክምናውን በተሻለ መልኩ ለመስጠት ስልጠናው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ዘላላም አይቸው ገልጸዋል፤እንዲሁም ከስልጠናው ተሳታፊ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሀኪሞች መካከል ዶ/ር እንዳልካቸው (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) እና ዶ/ር ጌጡ ድንቁ (ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ) ከዶ/ር ዘላላም አይቸው ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ እንዳላቸው ገልጸው የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ከዚህም በላይ ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡



