
የምርምር፣ የቴክኖሎጂ፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር የትኩረት መስኮች መመሪያ ሰነድ ረቂቅ ግምገማ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት አዲሱን ስትራቴጅክ እቅድ መሰረት ያደረገ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር የትኩረት መስኮች መመሪያ ሰነድ ረቂቅ ግምገማ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ሰኔ 01 እና 2 /2013ዓ/ም ተካሂዷል፡፡
በአውደ ጥናቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ፣ የአስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር ጋሻው አንዳርጌ፣ የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር መሰረት ካሴ፣ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር ተሰማ ዘውዴ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው፣ የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አዝመራው አየሁ፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ በአውደ ጥናቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከመለየቱ ጋር ተያይዞ በቅርቡ የአስር አመት ስትራቴጅክ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ፊት ሊያስፈነጥሩት የሚችሉ ትልልቅ ሃሳቦችን በመቀመር ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል፡፡ ይህንንም ለማሳካት በተለይ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የቴክንሎጂ ሽግግርና በሳይንስ ዘርፍ በሚቀጥሉት አስር አመታት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ቢኒያም አያይዘውም ባለፉት አምስት አመታት የዩኒቨርሲቲው የተጠቀመባቸውን የምርምር የትኩረት መስክ (thematic area)፣ ሌሎችን አሰራሮች፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ መመሪያዎችን በማጣጣም እና የዩኒቨርሲቲያችን አዲሱን የአስር አመት ስትራቴጅክ እቅድ መሰረት በማድረግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ባለፉት ወራት ስድስት ዶክመንቶችን ማለትም የምርምር የትኩረት መስኮች፣ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ፕሮጀክቶች አስተዳደር፣ የሳይንስ ሰቲም እና ኢንኩቬሽን ማእከል እና የአካል ጉዳትን አካቶነት መመሪያዎችን ረቂቅ መስራታቸውን ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም ዶ/ር ቢኒያም ከተዘጋጁት መመሪያዎች መካከል በመርሐ ግብሩ የሚቀርቡት ከመጀመሪያዎቹ አራቱ መመሪያዎች የሚታዩ እንደሆነና መመሪያዎች ላይ መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ዙሪያ በደንብ ግብአት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2007ዓ/ም ባወጣው የምርምር፣ የቴክንሎጂ ሽግግር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት መመሪያና የምርምር አጀንዳዎች በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቡን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን በመርሀ ግብሩ የመክፈቻ ንግግራቸው ያወሱ ሲሆን፣ ይህ የመመሪያ ረቂቅ አሁን ጊዜው የሚጠይቀውን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎችና ዩኒቨርሲቲው ያለበት የልዬታ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገና ተቋሙ የደረሰበትን አሁናዊ ሁኔታ ሊሸከም የሚችል መመሪያ ሊዘጋጅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ይህ መመሪያ የእርስ በእርስ መማማሪያ፣ ማህበረሰቡ የሚለወጥበት፣ ሀገሪቱ አሁን ያለባትን ውስብስብ ችግር የሚፈታ አቅጣጫ ስለሆነ ሁሉም ተሳታፊ በትኩረት እንዲሳተፍ አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻ ዶ/ር አስራት በመመሪያው ዝግጅት ላይ የተሳተፉ በየኮሌጁ የተወጣጡ መምሀራንን አመስግነው፣ የዚህ መድረክ ተሳታፊዎች ግብአት ታክሎበት የበለጠ የሚፈልገውን ውጤት የሚያስገኝ መመሪያ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡

በመቀጠልም በዶ/ር ፀጋው ፈንቴ ምርምር የትኩረት መስኮች መመሪያ ዙሪያ ገለፃ የቀረበ ሲሆን፣19 የምርምር መስኮችን፣ 15 የቴክኖሎጆ ሽግግር፣ 24 የማህበረሰብ አገልግሎት ረቂቅ መመሪያዎችን እንዳዘጋጁ ገልፀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዶ/ር አስማማው አለሙ እና በሌሎች ዲኖችና የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪዎች በምርምርና ህትመት፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ረቂቅ መመሪያዎች ዙሪያና በየኮሌጁ ተገምግመው የመጡ ረቂቅ መመሪያዎችን የግምገማ ግብረመልስ የየኮሌጆቹ ዲኖች በእለቱ ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡




