የምስጋና እና የዕውቅና ስነ-ስርዓት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል አስተዋፅኦ ላበረከቱ የተለያዩ አጋር አካላት የካቲት 14/2012 ዓ.ም የምስጋና እና የዕውቅና ስነ-ስርዓት መርሀ ግብር ተካሄደ፡፡
በመርሀግብሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የከንቲባው ተወካይ አቶ ተሾመ አግማስ፣ ከክልል፣ ከዞን እና ከከተማ አስተዳደር የመጡ የሥራ ሃላፊዎችና ተወካዮች፣ የጎንደር ከተማ የሰላምና ልማት ሸንጎ ፕዚዳንት አቶ ባዩህ በዛብህ ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንቶች፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ ሰራተኞች፣ የተማሪ ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
በ2012 በጀት አመት በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች በዩኒቨርሲቲው ቢያጋጥሙም የጎንደር ከተማ እና የአካባቢው ማህበረሰብ ዩኒቨርሲቲውን እንደ አይን ብሌኑ በመጠበቁ እንዲሁም ችግሩን ባለመጋራት እና ባለማባባሱ ዩኒቨርሲቲው ሰላሙን አስጠብቆ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማስቀጠሉ የመጀመሪያውን ወሰነ ትምህርት በሰላም ማጠናቀቁን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን መርሀ ግብሩን በንግግር ሲከፍቱ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ የዞን፣ የክልልና የፌደራል ተቋማት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ይህ ስኬት መምጣቱን ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው ይህንን የምስጋና መርሀ ግብር ማዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የነበረው ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እና ችግሩ ከመከሰቱ ቀድሞ መረጃዎችን በማድረስ፣ ተማሪዎችን በመምከር፣ በማስተማር፣ በመገፀስ፣ በማረጋጋት እንዲሁም ፀጥታውን በማስከበር የሀይማኖት አባቶች፣ የጎንደር ከተማ የሰላምና ልማት ሸንጎ፣ የተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች፣ የተማሪ አደረጃጀቶች፣ የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ ሰራተኞች፣ መምህራን፣ተማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የፀጥታ አካላት በመርሀ ግብሩ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡ በተጨማሪም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት ባለሙያዎችን በመላክ ለነበረው አስተዋፅኦ ምስጋና ቀርቧል፡፡
ፈጣንና ተአማኒ የሆኑ መረጃዎችን ወደ ማህበረሰቡ በማድረስ የተማሪ ወላጆች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ሌላው ማህበረሰብ እንዲረጋጋ ላደረጉ የመገናኛ ብዙሀን እንዲሁም የተከሰተው ችግር እንዳይባባስ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በተመሳሳይ በመርሀ ግብሩ ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡
በዚህ መርሀ ግብር የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የከንቲባው ተወካይ አቶ ተሾመ አግማስ እና የጎንደር ከተማ የሰላምና ልማት ሸንጎ ፕዚዳንት አቶ ባዩህ በዛብህ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በከተማው ያለ ብቸኛ ፋብሪካችን በመሆኑ አሁንም የዩኒቨርሲቲውን ሰላም በማስጠበቅ የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ለመደገፍ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ለነዚህ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ አደረጃጀቶች፣ የስራ ክፍሎች እና ማህበራት የምስጋና የሽልማት ወረቀት ተሰጥቶ፣ የሀይማኖት አባቶች ባደረጉት ቡራኬ እና የምረቃ መርሀግብ ተጠናቋል፡፡
ህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ደይሬክቶሬት



