የሥራ ፈጠራ ጥበብን፣ እውቀትንና ክህሎትን ለማሳደግ ሲሰጥ የነበረው የ2ኛው ዙር ስልጠና ተጠናቀቀ።
ዮኒቨርሲቲያችን በጎንደርና አካባቢው ለሚገኙ (በነጻነት ተጋድሎ ምክንያት በፖለቲካ እስር ቤቶች ለቆዩ፣ ከስራ ተፈናቅለው ለነበሩና ጉዳት ለደረሰባቸው) የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በሥራ ፈጠራ ጥበብና ተያያዥ ነጥቦች ትኩረት ያደረገው ይህ የ2ኛ ዙር ተመሳሳይ ስልጣና ዛሬ ጥር 4/2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተጠናቋል፡፡

ሰልጣኞች ዮኒቨርሲቲው ላደረገላቸው እገዛ አመስግነው በስልጠናው ከሥራ ፈጠራ ጥበብ ጋር የተያያዙ በርካታ ቁም ነገሮች እንደጨበጡ ግልጸዋል፡፡ በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት እንዲችሉ ደግሞ ለዩኒቨርሲቲውና ለሚመለከታቸው አጋር አካላት የትብብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህ መልካም ተሞክሮ በክልል እና በአገር ደረጃም እንዲሰፋ ጠይቀዋል።

“እናንተን ማገዝ ተቋማዊ ግዴታችን ነው፣ በምንችለው ሁሉ ከእናንተ ጎን ነን፡፡” ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን ናቸው፡፡ ዶ/ር አሥራት ዩኒቨርሲቲው ያለው ትልቁ ሀብት ዕውቀት መሆኑን አውስተው፣ ተጨማሪ ስልጠና ለመስጠትና ነጻ የትምህርት እድልን ለማመቻቸት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት እንደሚደረገውም በጤና በኩል እገዛና ድጋፍ ለሚሹ ግለሰቦች በተለይም በፖለቲካ አመለካከተቸው ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦች ተቋሙ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግላቸውም ገልጸዋል፡፡
በዚህ በጎ ተግባር ላይ ሌሌች ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻልም፣ ዩኒቨርሲቲው ልምድ በማጋራትና አብሮ በመሥራት በኩል ተጨማሪ ሥራ ይሠራል ብለዋል ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን፡፡



