
የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የሶስተኛ ድግሪ ስርዓተ ትምህርት ግምገማ አካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የትምህርት እቅድና ስራ አመራር ትምህርት ክፍል ሀገር አቀፍ የሶስተኛ ዲግሪ ስርአተ ትምህርት ግምገማ (Curriculum Review Work shop to launch PHD program in Education with specialization in Educational Policy and Planning, Educational Leadership and Management and Higher Education Administration ) አውደ ጥናት ሰኔ 29/2013ዓ/ም በማራኪ አልሙኒየም ህንፃ አካሄደ፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በአውደ ጥናቱ የመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት የተለያዩ ሀገራት እድገት በከፍተኛ ልዩነት ውስጥ የሚገኝበት ምክንያት ሀገራቱ ለትምህርት ባላቸው አመለካከትና ትግበራ ላይ መሆኑን በማውሳት በተፈጥሮ ሀብት ብቻ ለውጥ የሚገኝ ቢሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀብታም ትሆን ነበር ሆኖም ግን በትምህርት ያልበለፀግን በመሆናችን ድሃ ከሚባሉት ሀገራት ተርታ እንገኛለን እድገትና ለውጥ የሚመጣው በትምህርት በመሆኑ ሁላችንም ለትምህርት ትኩረት ልንሰጥ ይገባል፡፡ ዩኑቨርሲቲያችን የምርምር ዩኒቨርሰቲ ሆኖ መለየቱን ተከትሎ በድህረ ምረቃ ትምህርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ የሶስተኛ ግሪ መከፈትም ይህን የሚያጠናክር ነው፡፡ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ እንደ ዕድሜው ሳይሆን በርካታ የሚያኮሩ ተግባራትን እየፈፀመ የሚገኝ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ ለአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች እንደገለፁት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 11 ኮሌጆች ፣ 87 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞችን ፣ 134 የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን እየሰጠ ሲሆን ከ48 ሽህ በላይ ተማሪዎችንም እያስተማረ እንደሚገኝ በንግግራቸው አውስተው ይህ የሶስተኛ ድግሪ አውደ ጥናት በኮሌጁ ወስጥ የሚሠጡትን ትምህርቶች ከፍ የሚያድርግ ሲሆን ለጥናትና ምርምሩም ትኩረት እንደሰጠ አመላካች ነው ብለዋል ፡፡

የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር ክንዴ አበጀ በበኩላቸው የስነ-ትምህርት ኮሌጅ በ2003 ዓ.ም በሁለት የትምህር ክፍሎች የጀመረ ሲሆን አሁን ወደ አራት የትምህርት ክፍሎች ማደጉን አስረድተዋል፡፡ የስነ-ትምህርት ኮሌጅ ዋና ዓለማው ተወዳዳሪና በእውቀት የበለፀጉ መምህራን፣ ሱፐርቫዘሮች፣ የፖሊሲ አውጭዎች፣ የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ባለሙያዎችን እና የመሳሰሉትን በጥራት አስተምሮ ለሀገር ማብቃት መሆኑን በመግለፅ የሶስተኛ ድግሪ መርሃ-ግብር መከፈትም ለዚህ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኮሌጁ መምህራንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡