የቅድመና ድህረ- ምረቃ ካሪኩለም አተገባበርን የተመለከተ አውደጥናት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የትምህርት ጥራትና የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች በመተባበር የቅድመና ድህረ- ምረቃ ካሪኩለም አተገባበርን በተመለከተ የካቲት 9 እና 10/2013 ዓ.ም አውደጥናት ተካሄደ፡፡ በአውደጥናቱ የዩኒቨርሲቲው የህክምና ት/ቤት ስታፍ አባላት፣ የክሊኒካልና አካዳሚክ አስተባባሪዎች እንዲሁም የህክምና ማህበር ፕሬዚዳንትና ሌሎች በካሪኩለም ላይ ሰፊ ልምድ ያላቸው ባለሙያወች ተገኝተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ”ፓቶሎጅ”/Pathology/፣”ኒሮሎጅ”/Neurology/ እና “ኦርቶፔዲክስ”/Orthopedics/ አዳዲስ የህክምና ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች መክፈቱን የገለጹት የኮሌጁ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች አስተባባሪ ዶ/ር መኩሪያው አለማየሁ፣ የፕሮግራሞቹ መከፈት በአካባቢያችን እንዲሁም በሀገራችን ያለውን የስፔሻሊቲ ምሁራን እጥረት ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ መባሉ ይታወቃል፤ የምርምር ስራዎችን ለማስፋፋት ደግሞ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን ማስፋት ያስፈልጋል ፡፡ ስለሆነም የአውደ-ጥናቱ ዓላማ የካሪኩለም አተገባበርን ክፍተት በመለየት፣ በማስተካከልና በመተግበር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መሆኑን የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ አስተባባሪ ዶ/ር አበበ ሙጨ ገልጸዋል፡፡



