
የበይነ መረብ አጠቃቀም፣ ደህንነት፣ ስጋቶች እና መከላከያ መንገዶች ላይ ስልጠና ተሰጠ
በኢንፓክት አንፕሊፋየር ከሚደገፉ አለም አቀፍ ፕሮጀክቶች መካከልል አንዱ የሆነው የበይነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ፕሮጀክት (Online Safety Project) በባህርዳርና በደሴ ከተሞች ከሐምሌ 10/2013 እስከ ሐምሌ11/2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ከሚገኙ 45 የመንግስት እና የግል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለተመረጡ 90 የአይሲቲ መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን የፕሮጀክቱ አሰተባባሪና የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ም/ዲን የሆኑት ዶ/ር ተስፋማሪያም ሙሉጌታ ገለጹ፡፡
የፕሮጀክቱ አላማ በአማራ ክልል የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች ስለበይነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ስጋቶች ማለትም የሃሰት መረጃ ፥ የጥላቻ ንግግር ፥ የገንዘብ ማጭበርበር ፥ የበይነ መረብ አካውንት ነጠቃ ፥ የወሲብ ንግድ ፥ ፆታዊ ትንኮሳ እና የአሸባሪዎች ምልመላ እና ስለመከላከያ መንገዶች ያላቸውን ግንዛቤ እና ተጋላጭነት ማጥናት፣ ግንዛቢያቸውን ማሳደግ እና በሁለተኛ ደረጃ የአይሲቲ ስርዓተ ትምህርት የበይነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ስጋቶች እና መከላከያ መንገዶች እንዲካተቱ ማስገንዘብ መሆኑን ዶ/ር ተስፋማሪያም ገልፀዋል። በመቀጠልም በስምንት ምዕራፎች የተከፈለ የማስለጠኛ ሞጁል መዘጋጀቱን እና ከመስከረም 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በሚገኙ 45 ትምህርት ቤቶች ለተመረጡ 3600 የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች ስልጠናው እንደሚሰጥ ተገልፆል።
በስለጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ ብርሃኑ በላይ ጉዳዩ አሳሳቢ እና ወቅታዊ መሆኑን በመግለፅ ከስልጠና የሚያገኙትን እውቀት እና ክህሎት እራሳቸውን እና ተማሪዎቻቸውን ከበየነ መረብ አጠቃቀም ደህንነት ስጋቶች እንዲጠብቁ ለሰልጣኞች አሳስበዋል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ወቅታዊ የሆኑ ሃገራዊ እና ክልላዊ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠ የሚያደርገውን ጥረት በክልሉ ትምህርት ቢሮ ስም አመስግነው ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።