የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ “በአመራር የከፍተኛ ዲፕሎማ የድህረ-ምረቃ ”ሥርዓተ-ትምሕርት ዝግጅት ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኔጅመንትና ፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ትምህርት ክፍል “በአመራር በከፍተኛ ዲፕሎማ የድህረ-ምረቃ የሥርዓተ-ትምሕርት ግምገማ /Workshop on postgraduate Diploma in leadership / ተካሄደ ::

የሥርዓተ-ትምሕርቱን ውይይት በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ እንደገለፁት ይህ ዛሬ ለውይይት የቀረበው የአመራር ክሎትን የሚያዳብር ሥርዓተ-ትምህርት በባህሪው የተለዬ ነው ትምህርቱ ከመደበኛ የትምህርት መርሃ-ግብር ጋር አንድ አይነት ሳይሆን ረዥም ባልሆነ ጊዜ በተለዬ ዝግጅት የሚሰጥ ትምህርት ነው ብለዋል፡፡ በአብዛኛው በአመራር ቦታዎች ላይ የሚቀመጡ አካላት የዚህ አይነት የመምራት ክህሎት ትምህርትን የሰለጠኑ ባለመሆናቸውና ልምድን በማዳበር የሚሰራ በመሆኑ የዚህ ሥርዓተ-ትምህርት መዘጋጀት የአመራሩን ብቃት ከማሳደግ በተጨማሪም ስራን ውጤታማ አድርጎ ለማከናወን እድል ይሰጣልና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ይህን በማዘጋጀቱ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር ደርበው ቀኑብህ በበኩላቸው የኮሌጁን ጥሪ አክብረው ለመጡ እንግዶችና ተሳታፎዎች ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ “የአመራር ክህሎት” ትምህርት እንደ ሀገር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለው ኮሌጃችን በማመኑ ከፍተኛ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተን ዛሬ ለውይይት ይዘን በመቅረባችን ደስተኛ ነን ብለዋል፡፡ ይህ ሥርዓተ-ትምህርት የተለያዩ ተቋማት መሪዎችን አቅም በማጎልበት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ነው ፡፡ የአመራር ክህሎት ማደግ የስራ ቦታዎችን ምቹ በማድረግ ሰራተኞችን በጥበብ የመምራት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ በውይይቱ የተሻሉ ሃሳቦችን ጨምሮ ወደስራ እንገባለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡




