የባለ ድርሻ አከላት ሚና ለአማራ ክልል ዘላቂ የቱሪዝም ልማት በሚል መሪ ቃል አገራዊ ምክክር ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ከምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር #የባለ ድርሻ አከላት ሚና ለአማራ ክልል ዘላቂ የቱሪዝም ልማት$ በሚል መሪ ቃል አገራዊ ምክክር ከሰኔ 10-11/2011ዓ/ም ማራኪ አልሙኒዬም አዳራሽ አካሄደ፡፡
በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ፣ ከጠቅላይ ሚንስቴር ፅህፈት ቤት ተወካይ አቶ ወንድሙ ይርገዱ፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወ/ሮ አሰለፈች በቀለ እና ወ/ሮ ሞሚና ሙሀመድ፣ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛት አብዩ፣ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን፣ አቶ ስለሽ ግርማ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ም/ቢሮ ኃላፊ፣ የሀይማኖት አባቶች የዞንና ወረዳ የቱሪዝም ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች፣እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲን አጠቃላይ ገፅታና ዋና ዋና የስራ ተግባራትን አስተዋውቀዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠልም በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን በምስል አስደግፈው ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የዳበሩ ባለሙያዎችን በማፍራት፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ፣ የማህረሰብ አገልግሎቶችን በመስጠትና ሌሎች ዘርፉን የሚያሳድጉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ የዛሬው መድረክም ት/ት ክፍሉ እየሰራቸው ካሉ ታላላቅ ስራዎች መካከል እንደማሳያ ሊወሰድ እንደሚችል አውስተው፣ በቱሪዝም ባለ ድርሻ አካላት መካከል ያለውን የትብብርና የስራ ግንኙነት እንደሚያሳድግና ለዘርፉ እድገት የሚያግዙ አዳዲስ ሀሳቦች የሚወጡበት መርሀ ግብር እንደሚሆን ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልፀዋል፡፡
ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከአ/ብ/ክ/መ የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን በተገኙ በአቶ አብርሃም ማናዬ፣ በአ/ብ/ክ/መ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ጥበቃና ልማት ወቅታዊ ሁኔታና የወደፊት እጣ ፈንታ የሚል ጥናት፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር በሆኑት በአቶ የኔሰው አለነ ደግሞ በአ/ብ/ክ/መ የሚገኙ ሰው ሰራሽ ቅርሶች ወቅታዊ ሁኔታ፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ ጥናት ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም በተጓዥ ጋዜጠኛው በሄኖክ ስዩም ደግሞ የሚድያ ሚና ለቱሪዝም ሀብት ጥበቃና ልማት የሚል ጥናት ቀርቦ ጽሁፎችን መነሻ በማድረግ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደረጎባቸው፣ የሚመለከታቸው አካላትና ሀላፊዎችም ለጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የስራ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል፡፡
ሰኔ 11/2011ዓ/ም ደግሞ በጎርጎራና በአካባቢው የሚገኙትን የአፄ ሱስኒዮስ ቤተ-መንግስትን፣ የማን እንደ አባ ገዳምን እና የደብረሲና ማሪያምን ቤተ ክርስቲያን በመጎብኘት ቅርሶቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማስተዋልና ለመገምገም ተችሏል፡፡ ጉብኝቱን እና አጠቃላይ የነበረውን የምክክር ቆይታ አስመልክቶ በጎርጎራ መዝናኛ አዳራሽ ውስጥ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን መወጣት እንደሚገባውና ማህበረሰቡን የቱሪዝም ልማት ባለቤት እንዲሆን ማድረግ እና ከልማቱም ተጠቃሚ እንዲሆን መሰራት እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም ፕ/ር መርሻ ጫኔ የፕሮግራሙን መዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ከህግ አውጭው እስከ ፈፃሚ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በመሆኑ ችግሮች በአግባቡ የተለዩበት፣ ወደፊት ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት ቁርጠኝነቱንና ቁጭቱን ያሳየበት እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በአካባቢያችን ያሉ ቅርሶችንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በቅድሚያ ማወቅ እንደሚገባ፣ ከታወቁ ደግሞ ለማስተዳደር፣ የተጎዱትን ለመጠገን፣ ጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉትን ደግሞ ባሉበት እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደሚረዳ አውስተው ዩኒቨርሲቲው በቅርሶች ጥገናና እንክብካቤ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚፈፅም ቃል ገብተዋል፡፡



