የተጎዱ መሬቶችን ለማገገምና የደን ልማትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የደን ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ለወገራ ወረዳ አርሶ አደሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዶ/ር አስማማው አለሙ አስተባባሪነት ከኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ሴክተር ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት በተገኘ የበጀት ድጋፍ Restoration of sacred forests and degraded forest landscaps for enhanced carbon sequestration, biodiversity conservation and livelihood improvements( RSDL-CCLI) በሚል ርዕስ በዩኒቨርሲቲያችን እየተተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
እነዚህን የደን ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ለወገራ ወረዳ አርሶ አደሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ግንቦት 3 እና 4/2015 ዓ/ም በወገራ ወረዳ ኮሶዬ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሽ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የደን ሳይንስ ት/ክፍል መምህራንና ተመራማሪዎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በዚህ የስልጠና መርሃ ግብር የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ከሃሊ ጀንበሬ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው መኩሪያው፣ የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር አስማማው አለሙ፣ የወገራ ወረዳ ግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ምስጋናው ታከለና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በወገራ ወረዳ በተለይም በኮሶዬ አካባቢ በርካታ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ያነሱት የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ከሃሊ ጀንበሬ፣ በአካባቢው የተፋሰስ ልማትን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማለማመድና ለማሳፋፋት እየተሰራው ያለውን ትልቅ ስራ አድንቀዋል፡፡ የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከባለፉት 3 እና 2 ሁለት ዓመታት ጀምሮ ወረዳው ላይ አኬሻ ዲከረንስ የሚባለውን ዛፍ ቀድመው እንዳስገቡ ዶ/ር ከሃሊ አያይዘው ያወሱ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂውን ለማስፋት እየተሰራው ያለውን ስራ ማህበረሰቡ ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በተለያም ከደን ሃብት ጋር ተያይዞ ዘርፈ ብዙ የሆነ አገልግሎት የሚሰጠውን፣ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ፣ ለእንስሳት ምግብነትና ለማገዶ በተለይም ለከሰል አገልግሎት የሚውለውን የአኬሻ ዲከረንስን( የፈረንጅ ፅድ) ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ሰልጣኝ አርሶ አደሮቹ በተነሳሽነት እንዲያለሙና እንዲያስፋፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው መኩሪያው በአደረጉት የመክፈቻ ንግግር የገለፁ ሲሆን፣ በቀረቡት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ የሚሰጠውን ስልጠና በአግባቡ በመውሰድ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደው የማሰልጠን ኃላፊነት እንደተጣለባቸውም አበክረው ተናግረዋል፡፡
በመቀጠል የደን ሳይንስ መምህርና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ በሆኑት በዶ/ር አስማማው አለሙ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ገለፃ የቀረበ ሲሆን፣ የተጎዱ መሬቶችንና የተጎዱ ደኖችን በተለይም በአብያተ ክርስቲያናትና በተፋሰስ አካባቢ ያሉ የተጎዱ መሬቶችን ለማገገምና የደን ልማትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የደን ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተፋሰሶች ማስገባት ላይ ዓላማ ያደረገ ፕሮጀክት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ለዚህም በጣም ፈጣን እድገት ያለው፣የገቢ ምንጭ የሚሆን ( ለከሰልና ለማገዶ እንጨት)፣ ናይትሮጅን የተሰኘውን ማዕድን መሬት ላይ እንዲኖር የሚያደርግ፣ ቅጠሉ ሲረግፍ የአፈር ለምነትን የሚፈጥርና መጨረሻም ከተቆረጠ በኋላ ወዲያውኑ አርሶ ለሰብል መሬት መጠቀም እንዲቻል የሚረዳውን የአኬሻ ዲከረንስን( የፈረንጅ ፅድ) ማስፋፋት አንደኛው ቴክኖሎጂ እንደሆነ ዶ/ር አስማማው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጠዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መገጤ ከተባለው ተፋሰስ ላይ እርከን ከተሰራበት መሬት ላይ የእንስሳት መኖና የገቢ ምንጭ የሚሆኑ እንደ ጌሾና ሌሎች ፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል በዘላቂነት ውጤታማ ማድረግ፣ በማሳ ውስጥ ደግሞ በተፈጥሮ የበቀለውን ዛፍና ችግኞችን እንዴት ተንከባክቦ ማሳደግና ከሰብል ጋር ማቀናጀት ይቻላል የሚሉትን ቴክኖሎጂዎች ማጠናከር ላይ የሚሰሩ ስራዎችንም ዶ/ር አስማማው በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ወደፊትም በጓሮና ውሃ ገብ በሆኑ አካባቢዎች የአፕል ችግኞችን በማሰራጨት የማልማት ስራ እንደሚሰራና ሌሎችን በቀጣይ የሚሰሩ ተግባራትን አክለው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በኮሌጁ የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህራንና ተመራማሪ በሆኑት በአቶ ዮሀንስ ገብረማሪያም፣ በአቶ ኪሩቤል ሞትባይኖርና በአቶ ሙሀባው ታጁ የተሰጠ ሲሆን፣ ስለ አካሽያ ዲከረንስ ውድሎት ተከላ፣ አያያዝና አጠቃቀም፣ ተፋሰስን ገቢ በሚያስገኙ በስነ ህይወታዊ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ዘዴ ማጠናከር የማሳ ውስጥ ዛፍ ተከላ፣ እንክብካቤና አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም አጠቃላይ ውይይት በማካሄድና ሰልጣኞቹ በአካሽያ ዲከረንስ ውድሎት የለሙ አካባቢዎችን በመጎብኘት መርሃ ግብሩ ተጠናቋል፡፡