የቱሪዝም ሃብት ልማትና ቅርስ ጥበቃ ጠቀሜታን የተመለከተ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ጎንደር ዞን ጃን አሞራ እና በየዳ ወረዳዎች የቱሪዝም ሃብት ልማትን ለማጠናከር እና የቅርስ ክብካቤን ለመደገፍ ያስችላል የተባለለትና ከየካቲት 9 እስከ 11/2012 ዓ.ም የሚቆይ ስልጣና በመካነ ብርሃን እና ድል ይብዛ ከተማ ለባለድርሻ አካላት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በየዳ እና ጃን አሞራ ወረዳዎች ታላቁን የራስ ደጀን ተራራ ተንተርሰው በሰሜን ሰንሰለታማ ተራሮች የሚገኙ ወረዳዎች ሲሆኑ በርካታ ሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦች ይገኙባቸዋል፡፡ ይሁን እንጅ በወረዳዎቹ የሚገኙ ቅርሶች ከባለድርሻ አካላት የግንዛቤ እጥረት እና ከአካባቢው መሰረተ ልማት አለመሟላት በሚመነጭ ችግር ምክንያት ጎብኝዎች ወደ አካባቢው ሲያዘወትሩ አይስተዋልም፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ እና የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት በማሰብ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ለሶስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና ለሃይማኖት አባቶች፣ለቱሪዝም ባለሙያዎች፣ለታዋቂ ሰዎች፣ወጣቶች እና ለጽ/ቤት ሃላፊዎች ስልጠና በመስጠት ላይ ነው፡፡
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ በወረዳዎቹ በርካታ የተፈጥሮ ሃብትና ሰውሰራሽ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ቢኖሩም የአካባቢው ማህበረሰብ በአግባቡ ሳይጠቀምበት በመቆየቱ ስልጠናው ማስፈለጉን ለተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ፕረፎሰሩ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ለሌሎች በርካታ አካባቢዎች የሚሰጠውን ሁሉን አቀፍ የማህበረሰብ አገልግሎት በመሰረተ ልማት ችግር ምክንያት አገልግሎትና ድጋፍ ሳያገኙ የቆዩ ራቅ ያሉ ቦታዎችን ለመድረስ አቅዶ በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸው ወረዳዎች ያላቸውን የተለያየ ሃብት እንዲለዩ(እንዲያውቁ) እና ሀብቶቻቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ የማህበረሰብ አገልግሎቱ ዋነኛ አላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጃናሞራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደርበው መለስ እና የበየዳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደገኝ ውብአየሁ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው እየሰራ ያለውን ስራ አድንቀው ለስራው መሳካትም ወረዳዎቹ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታው በየዳና ጃናሞራ ወረዳዎች ላይ ያሉ የቱሪስ መስህቦችን በተለይም የቅርሶች ደህንነት በተጠበቀ መልኩ ለጎብኝዎች እይታ የሚበቁበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የግንዛቤ ክፍተቶችን ለመሙላት የታቀደለት ስልጠና መሆኑን ገልጸው ለወደፊትም በአካባቢው ባለው የቱሪዝም ልማት ላይ ዩኒቨርሲቲው ከወረዳዎች ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡



