የቴክኖሎጂ ኢነስቲትዩት ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን አከበረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ110ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ለ45 ጊዜ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲአችን ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን (march 8) በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሮ ውሏል፡፡ በዓሉ የተከበረው መጋቢት 5/2013 ዓ.ም ሲሆን መሪ ቃሉም “የሴቶችን መብት የሚያከብር ማህበረሰብ እንፍጠር” የሚል ነበር፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን የተለያዩ ሀገራት በተለያየ ሁኔታ ቢያከብሩትም በዋናነት ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በማህበራዊ ሁኔታዎች እኩል ተጠቃሚነታቸውንና ተሳትፎአቸውን እውቅና በመስጠት እንደሚያከብሩ ዋቢ አድርገው የተናገሩት የቴክኖሎጂ ኢስቲትዩት ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቡድን መሪ ወ/ሮ ጉልቴ በለጠ ናቸው፡፡ በበዓሉ የህግ፣ የሰብአዊ መብታቸውን ነጻነታቸውን ለማስከበር እንዲሁም ጾታዊ ጥቃትን ለማስቀደም የሚደረግ ትግል እንደሚዘከር ወ/ሮ ጉልቴ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

የዕለቱ ስነ-ስርአት በዩኒቨርሲቲው ኪነትና ባህል ማእከል( ኪ.ባ.ማ) አባላት በሙዚቃና በድራማ ደምቆ ተከብሯል፡፡ በመጨረሻም በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት የቴክኖሎጂ ኢንስቱትዩት ተማሪዎች የማበረታቻ የምስክር ወረቀት በኬሚካል ምህንድስና መ/ርት አሻገር ሽመላሽ (የበዓሉን መርሀ-ግብር በንግግር የከፈቱ) አማካኝነት ተበርክቶላቸዋል፡፡




