የንጹህ መጠጥ ዉሃ ማጣሪያ ማሽን ስራ ጀመረ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በለሳ (ምስራቅና ምዕራብ) ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለረዥም አመታት በንጹህ የመጠጥ ውሀ ችግር ምክንያት ለበርካታ እንግልትና ተያያዥ ችግሮች ተጋላጭ ሲሆኑ ቆተዋል፡፡

በመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከእስራኤል ኢምባሲ ያገኘውን የመጠጥ ውሃ ማጣሪያ ከሰቆጣ የቃልኪዳን ስምምነት ጋር በመተባበር በምስራቅ በለሳ ወረዳ አዱራራ ወርቀሰቀል/ቀበሌ 33/ አካባቢ ለሚኖሩ እና በመጠጥ ውሃ እጥረት የተቸገሩ እና ውሃ ለመቅዳት ከ3 ሰአት ያላነሰ የእግር ጉዞ ይጓዙ ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የመጠጥ ውሃ ማጣሪያ እንዲገጠምላቸው በማድረግ የንፁኃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በዚህ ቀበሌ ውስጥ እንደ አቶ በላይነው ተስፋሁን (የቀበሌው ስራ አስኪያጅ) ገለጻ ከ5000 በላይ ህዝብ ወይም1380 አባዋራ የሚኖር ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት 540 አባዋር ወይም 3240 የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ ናቸው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በወረዳው ከ 12 ያላነሱ የውሃ ግድቦት ያሉ ቢሆንም ለመጠጥ ውሃ አገለግሎት ይውሉ ዘንድ ማጣሪ የተገጠመለት ግፍብ በዚህ ቀበሌ የተሰራው ግድብ ብቻ ነው፡፡

በእለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበተሰብ አገልግሎት ም/ፕረዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ፣ የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገለግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው፣ የፌድራል የሰቆጣ ቃልኪዳን አስተባባሪ አቶ መስፍን ጎበና፣ የክልል የሰቆጣ ቃልኪዳን አስተባባሪ አቶ አወቀ እጅጉ እንዲሁም፣ ስራዉን ሲከታተሉ የነበሩ የዩኒቨርሲቲው መመህራን ( አቶ ስንታየሁ ዳባ እና ሙላት ገ/ሂወት) እና ከእስራኤል የመጡ ቴክኒሻኖች ተገኝተዋል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብም የውሃ ማጣሪው ተገንብቶ ለአገለግሎት በመዋሉ ከፍተኛ ደስታ እደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

የዉሃ ማጣሪያውን የእስራኤል ኢምባሲ በነጻ ያቀረበው ሲሆን በሰአት እስከ 2000 ሊትር ድረስ ዉሃ የማጣራ አቅም ሲኖረው ከ5 አመት በላይ የማገለገል አቅም አለው፡፡ ማጣሪው በጸሃይ ብርሃን ጎልበት (solar energy) በመጠቀም የሚሰራ ሲሆን የማጣራት ሂደቱ በተፈለገው መልኩ እንዲሄድም በየ እለቱ የእጥበት ስራ ( back wash) የሚደረግለት ሲሆን በወር አንድ ጊዜ በኬሚካል/ክሎሪን እጥበት ይደረግለታል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የእስራኤል ኢንባሲን እና በዚህ ስራ ሲሳተፉ ለነበሩ ባለሙያዎች ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡



