የአለም የደን ቀን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ተከብሮ ዋለ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የጠቅላላ ደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል March 21 የሚከበረውን የአለም የደን ቀንን Forest Restoration: A path to recovery and well-being በሚል መሪ ቃል በኮሌጁ አልጣሽ አዳራሽ መጋቢት 16/2013ዓ/ም በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡
በዕለቱ የኮሌጁ ዲን ተወካይ ዶ/ር የኑስ ኡስማን ጨምሮ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት በትምህርት ክፍሉ መምህራን የመነሻ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፣ ደንና የሰው ልጅ ህይወት እንዲሁም የአለም አቀፍ የደን ቀን ላይ ያተኮረ ገለፃ በመ/ር ዳግም ፍቅር፣ በኢትዮጵያ የደን ሀብትና የደን መልሶ ማልማት በዶ/ር አስማማው አለሙ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የአረንጓዴ ንቅናቄ በኢትዮጵያ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ2012ዓ/ም ችግኝ ተከላ ተሞክሮ በሚል የቀረበ ጽሁፍ በመ/ር ብርቱካን አስሬ ቀርቦ ስለ ደን ሀብት ጥቅም እና እንክብካቤ አስፈላጊነት ግንዛቤ መፍጠሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡


የጠቅላላ ደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ በደን ልማት ዙሪያ የዘር ለቀማና አቅርቦት፣ ችግኝ ማፍላትና ማሰራጨት፣ የምርምር ጣቢያ ልማት ( በጎርጎራ፣ በሽንታና በበለሳ)፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እነደሚሰጥ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ዳግም ፍቅር ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም በመተማ በቋራና በጎንደር ዙሪያ አካባቢ የተሰበሰቡ የፍራፍሬ ዘሮች እንዲሁም የጣውላ ምርቶች ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች አስተዋውቀዋል፡፡





