የአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ የአረንጓዴ መቀነትነቱን ጠብቆ እንዲቆይ የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ
ቋራና አካባቢው የበርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት እንደሆነ በተለያዩ ጥናቶች ቢረጋገጥም ሆኖም የአከባባቢው ማህበረሰብ ባሉት የተፈጥሮ ሀብቶች የሚገባውን ያህል እንዳልተጠቀመ ይታመናል፡፡ ስለሆነም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደ ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን በመቅረጽና ጥናትና ምርምሮችን በስፋት በማካሄድ የቋራና የአካባቢውን ህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል ባሉት በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎችና ብዝሀ ህይዎቶች እንዲሁም በሚሸፍነው መልክዐ-ምድር በሀገራችን በግምባር ቀምትነት ከሚጠቀሱ ብሄራዊ ፓርኮች አንዱ የሆነው የአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ (አረንጓዴው መቀነት/ቀበቶ(The Green Belt) ተገቢውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲደረግለት እንዲሁም በመንግስት ደረጃ እውቅናና ትኩረት እንዲያገኝ በተቋምና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ አውደ-ጥናቶችንና ምርምሮችን አካሂዷል፡፡
በተመሳሳይ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች የተሰሩ የምርምር ስራዎችን መነሻ በማድረግ ፓርኩ የአረንጓዴ መቀነትነቱን እንደያዘ እንዲቀጥል ዓለማው ያደረገ ስልጠና ለቋራ ወረዳ ግብርና ሙያተኞች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መጋቢት 25 እና 26/2013 ዓ.ም በደለጉ ከተማ ሰጥቷል፡፡

ይህን ስልጠና በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱት የቋራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤፍሬም ወርቁ ሲሆኑ በንግግራቸውም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለወረዳው የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አውስተዋል፡፡ በተለይም ማህበረሰቡ በወረዳው ካሉት የተፈጥሮ ገጸ-በረከቶች በዋናነትም ከአልጣሽ ቢሄራዊ ፓርክ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን በዩኒቨርሲቲው ለሚያደርጉት ተጨባጭ ድጋፎች በወረዳው ህዝብ ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዓሳና የንብ ሀብት ልማት አቅም፣ ተግዳሮቶችና አዋጭነት፤ ዋና ዋና የንብ በሽታዎች፤ የአሳ ምርት አመራረት፣ አያያዝና አጠቃቀም፤ የእንስሳት መኖ አሰባሰብ፣ አያያዝና አጠቃቀም የሚሉትና የመሳሰሉት በስልጠናው በስፋት የተዳሰሱ ሀሳቦች እንደሆኑ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መኩሪያው ዘውዴ ገልጸዋል፡፡
የቋራ ወረዳና የአካባቢው ህዝቦች ከላይ በተጠቀሱት በግብርናና በመሳሳሰሉት ልማቶች የራሳቸው የሆነና ወጥነት ያለው የገቢ ምንጭ ማግኘት ከቻሉ፣ በተጓዳኝ ለአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ መጠበቅ ቀጥተኛ የሆነ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው አቶ መኩሪያው አያይዘው ተናግረዋል፡፡ ማህበረሰቡ ከፓርኩ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው በልዩ ሁኔታ ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙና ቀጣይነት ያላቸው ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም በአስተባባሪው ተገልጿል፡፡

በስልጠናው ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል ነዋሪነታቸው በቋራ ወረዳ በርሜል ቀበሌ የሆኑትና በንብ ማነብ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ አለምየ ስዩም ይገበኙታል፡፡ አቶ አለምየ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ ለሚሰጣቸው በሳይንስ የተደገፉ ተግባር ተኮር ስልጠናዎች በበኩላቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡



