
የአማራ ጥናት ተቋም ረቂቅ ሰነድና የሀገርኛ ቋንቋዎች ሥርዓተ ትምህርት መመስረቻ የፍላጎት ጥናት ሰነድ ግምገማ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአማራ ጥናት ተቋም ረቂቅ ሰነድና የሀገርኛ ቋንቋዎች ሥርዓተ ትምህርት መመስረቻ የፍላጎት ጥናት ሰነድ ግምገማ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ዛሬ ሚያዚያ 24/2015ዓ/ም በማራኪ አልሙኒዬም ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሄደ፡፡
በዚህ ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት የዩኒቨርሲቲያችንን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይንን ጨምሮ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተገኙ የፕሬዚዳንት ተወካዮች ዲኖች፣ የዩኒቨርሲቲያችን ከፍተኛአመራሮች፣ ዲኖች፣ዳይሬክተሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለልህቀት እንተጋለን በሚል መሪ ቃል በተመረጡና የሰው ኃይል ክፍተት ያለባቸውን ዘርፎች በመለየት አዳዲስ የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች በመስጠት፣ በርካታ ምርምሮች በማካሄድና በምርምር ላይ የተመሰረቱ ችግር ፈቺ የቴክኖሌጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በፍጥነትና በሙያዊነት እያከናወነ እንደሚገን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡ በዕለቱ ምክክር የተደረገባቸው ሰነዶች ማለትም የአማራ ጥናት ተቋም ረቂቅ ሰነድና የሀገርኛ ቋንቋዎች ሥርዓተ ትምህርት የፍላጎት ጥናት ሰነዶች ወደ ተግባር ሲገቡ የሀገራችን ባህል፣ ታሪክ፣ወግ፣ትውፊት፣ቋንቋ የአኗኗር ዘይቤና የመሳሰሉትን በተገቢው ከማሳወቅና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ ፋይዳቸው የጎላ እንደሆነ ዶ/ር አሥራት አክለው ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አሥራት አያይዘውም ከዳሰሳ ጥናትና ሰነድ ዝግጅት ጀምሮ አስካሁን ድረስ በሙያና በማስተባበር ደፋ ቀና ሲሉ ለነበሩ ለአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ለማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብዕ ኮሌጅና ለሌሎች ሃላፊዎችንና መምህራንን ያመሰገኙሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው አመራርም ሁሉንም የሚጀመሩ ፕሮግራሞች ዕውን እንዲሆኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲያችን የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ በበኩላቸው የፕሮግራሙን አስፈላጊነት በመርሃ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ የአማራ ጥናት ተቋም መመስረት የአማራን ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ወግ፣ትውፊት፣ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ ወደ ሀብት ከመቀየር አኳያ፣ በአብዛኛው ቃላዊ የሆኑ የታሪክ ክፍሎችን በመሰነድ ከትውልድ ትውልድ ከማስተላለፍና ያለንን ጥልቅ ባህልና ታሪክ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናትና በመሰነድ ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች የዓለም ህዝቦች ከማስተዋወቅ፣ በተለያዩ ጊዚያት በአማራ ህዝብ ላይ የሚነገሩ አሉታዊ ትርክቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እውነት አለመሆኑን በማረጋገጥና ከሌሎች ብሄርብሄረሰቦች ጋር በጋራ በመሆን ኢትዮጵያን ወደፊት መራመድ ከማስቻል አንፃር የተቋሙ መመስረት ያለውን ፋይዳ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በመቀጠል የአማራ ጥናት ተቋም ረቂቅ ሰነድ ላይ ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በተወጣጡ የውስጥ ገምጋሚዎች፣ ከፖለቲካል ሳይንስ አስተዳደር ጥናት ዶ/ር ባምላክ ይደግ፣ ከባህል ጥናት አቶ እምወደው መልከኛው፣ ከታሪክና ቅርስ ጥናት ረ/ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ተሻገር ሃብቴ ግምገማ የቀረበ ሲሆን፣ ከሀገር ውስጥና ውጭ የሚገኙ የውጭ ገምጋሚዎች የሰጧቸው ገንቢ ሃሳቦች በዝርዝር ቀርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ በሀገርኛ ቋንቋዎች ሥርዓተ ትምህርት ማቋቋሚያ ሰነዶች የውስጥ ገምጋሚ በሆኑት በመ/ር ሙሉቀን ዘመነ ግምገማ የቀረበ ሲሆን፣ በውጭ ገምጋሚዎች በፕ/ር ባዬ ይማም (በመ/ር ሙሉቀን ዘመነ በኩል)፣ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ዲን በሆኑት በአቶ ሀቢብ መሀመድና ከአፋርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል በአቶ አብደላ አጋህሊና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የኦሮምኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊ በሆኑት በአቶ ተፈሪ ግምገማው ቀርቧል፡፡
በሀገርኛ ቋንቋዎች ሥርዓተ ትምህርት ማቋቋሚያ ረቂቅ ሰነድ ላይ በውስጥና በውጭ ገምጋሚዎች የቀረበውን ግምገማ ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰጥተውና ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብዕ ኮሌጅ በእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር፣ የኮለጁ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪና የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር በዛብህ ተስፋሁነኝ በበኩላቸው በቀረቡት ረቂቅ ሰነዶች ላይ የሚመለከታቸው በዘርፉ ትልቅ ልምድ ያካበቱ የውስጥና የውጭ ገምጋሚዎች ሃሳባቸውን አዋጥተውና በልፅጎ ተቋሙንና ትምህርት ክፍሎችን በቅርብ ጊዜ ዕውን ለማድረግ ታስቦ መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱን አስመልክቶ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል፡፡ የሀገረኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍሎችን በማቋቋም በኩልም በዋናነት አራት ሀገርኛ ቋንቋዎችን ማለትም ትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛና አፋርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍሎችን በማደራጀት በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሰጡ ለማስቻል ዓላማ ያደረገ ፕሮግራም እንደሆነም ዶ/ር በዛብህ አክለው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ውስጥ የኦሮምኛ ቋንቋ የላቲን ስክሪፕት የሚጠቀም ቢሆንም ከዚህ በጨማሪ እንደ አዲስ የኢትዮፒክ ስክሪፕትን በትይዩ በመጠቀም ቋንቋውን በሁለት መንገድ ማስተማር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ዶ/ር በዛብህ አያይዘው ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻ በኮሌጁ ዲን በዶ/ር አገኘሁ ተስፋ የመዝጊያ ንግግር መርሃ ግብሩ ተጠናቋል፡፡