የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊቲ ፕሮግራም ለመክፈት የውስጥ የስርአተ ትምህርት ግምገማ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ በስነ-አእምሮ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊቲ ፕሮግራም “PSYCHIATRY RESIDENCY PROGRAM” ለመክፈት የውስጥ የስርአተ ትምህርት ግምገማ ሰኔ 10/2013 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ ተካሄደ፡፡

በዚህ የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊቲ የግምገማ ፕሮግራም የተለያዩ የኮሌጁ ማህበረሰብ አባላት፣ የስራ ኃላፊዎች እና የትምህርት ክፍሉ መምህራን ተገኝተዋል፡፡ የህ/ጤ/ሳ/ኮሌጅ አካዳሚክ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ፣ እንደ አንድ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተቋማችን ይህን የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት መስጠቱ ከአእምሮ ችግር አንጻር ታላላቅ ችግር ፈች ምርምሮችን በመስራት ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ሀሳቦችን ለማፍለቅ እንደሚረዳ ገልጸዋል፤ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ አስር አመታት ውስጥ አንድ ትልቅ የእእምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል ለመስራት ማቀዱንም አብራርተዋል፤በግምገማ ሂደቱ አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙትን አካላትም አመስግነዋል፡፡

የስነ አዕምሮ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ጎሹ ኔንቆ፣ ከፕሮግራሙ ጋር በተያያዘ በስርአተ ትምህርት ግምገማ የተሻለ ልምድና እውቀት ያላቸው የዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎችና ምሁራን ያላቸውን ምክረ ሀሳብ ለማካተት ታስቦ የግምገማ አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፤ በመጀመሪያው ዙር ምክረ ሀሳብ መሰረት በስርአተ ትምህር ላይ አስፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎ በቀጣይ ለውጭ ገምጋሚዎች እንደሚቀርብም አብራርተዋል፡፡




