የአየር ንብረት ለውጥን ባገናዘበ የእንስሳት እርባታ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የአየር ንብረት ለውጥን ያገናዘበ የእንስሳት እርባታ ምን መምሰል አለበት በሚል ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለተውጣጡ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶአደሮች እና ዘመናዊ የወተት ላም አርቢዎች በአምባ ጊዎርጊስ ከተማ መጋቢት 3 እና 4/2013ዓ.ም ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ደ/ር አንዋር ኑሩ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታትና ኑሮውንም ለማሻሻል በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው አሁንም የአየር ንብረት ለውጥን ያገናዘበ ውጤታማ የእንስሳት እርባታ እንዲካሄድ ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ወ/ሮ ፍሬህይወት አለሙ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥን ያማካለ የእንስሳት እርባታ ዘዴን፣ የተሸሻሉ የመኖ ዝርያዎችን በማምረትና በመመገብ ፣ የአየር ንብረት ለውጡን መቋቋም የሚችሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በመምረጥና በማርባት እንዲሁም የእንስሳትን ፅዳጅን እንደገና በባዮ ጋዝ መልኩ በመጠቀም እንስሳት በአየር ንብረት ለውጡ ላይ የሚኖራቸውን ከፍተኛ ሚና ለመቀነስ አላማ ያደረገ ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ያገናዘበ የእንስሳት እርባታ፣ የአየር ንብረት ለውጡን ያማከለ የእንስሳት መኖ አመራረት እና አመጋገብ፣ የአየር ንብረት ለውጡን ያማከለ የወተት ግብይት ስርዓት በሚሉ እና ተያያዝ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አተኩሮ ተሰጥቷል፡፡
ተመሳሰሳይ ይዘት ያለው ስልጠና በሰሜን ጎንደር ዞን ለተውጣጡ አካላትም ከዛሬ መጋቢት 6 ጀምሮ በደባርቅ ከተማ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡



