የአይን ህክምና ዘመቻው አድማሱን በማስፋት ተጠናክሮ ቀጥሏል
በጤና ዙሪያ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ በርካታ መንግስታዊና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ቢኖሩም፣ የመንገድ መሰረተ ልማት እምብዛም ባልተሟላባቸው አካባቢዎች በቂ የጤና አገልግሎት መስጠት ላይ ውስንነቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡
ይህንንም በመረዳት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የህክምና ሙያተኞች ከአጋር ግብረ-ሰናይ አካላት ጋር በመተባበር በያዝነው ግማሽ የበጀት ዓመት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ አስር ወረዳዎች ከ50, 000 በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አጠቃላይ የዐይን ህክምና መከናወኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህ ተመሳሳይ ህክምና( የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ህክምና፣ የመድሀኒት ህክምና፣ የዓይን ቆብ መቀልበስ ቀዶ ህክምናና የመነጸር ልኬታ) በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ በሚገኘው ወገዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከየካቲት 16 -18/2012 ዓ.ም ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎቱ ተሰጥቷል፡፡

ለስማዳ ወረዳና ለአካባቢው ማህበረሰብ የነጻ የዓይን ህክምና ለመስጠት ቃል በገባነው መሰረት ለ2ኛ ጊዜ በመምጣት አገልግሎቱን መስጠት ችለናል ያሉት የዩኒቨርሲቲው ኦርቢስ ኢንተርናሽናል አስተባባሪ አቶ ሰማልኝ አበው ናቸው፡፡ በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ባልተሟላላቸውና የህክምና አገልግሎቱ ተደራሽ በማይሆንባቸው አካባቢዎች ለመድረስ ዩኒቨርሲቲው አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስተባባሪው አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ዘመቻ (በስማዳ ወራዳ) 2751 ጠቅላላ የአይን ህክምና የተደረገ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 1093 ጠቅላላ የመድሐኒት ህክምና፣ 134 የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ህክምናና 19 የዓይን ቆብ መቀልበስ ህክምና መደረጉን አቶ ሰማልኝ ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪው የህክምና ቡድናቸውን አመስግነዋል፤ የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት ለሚያደርገው ክትትልና ድጋፍም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ፈንታው ቦታው ድረስ በመሄድ የህክምና ቡድኑን ስራ በማድነቅ አበረታተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የዓይን ህክምና ሙያተኞች በቀናነትና በፍላጎት የግል ጥቅማቸውን ችላ በማለት ማህበረሰባቸውን በሙያቸው ለማገልገል በመቻለቸው በፕ/ር መርሻ በኩል ልባዊ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት በቀጣይ ለሚደረጉ ዘመቻዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአጋርነት እንደሚቀጥልም ም/ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡

በቀላሉ የህክምና አገልግሎት በማይሰጥበት ሁኔታ የነበሩ የስማዳ ወረዳና የአካባባው ህሙማን፣ የዓይን ብርሀናቸውን በከፊልና በሙሉ አጥተው ለረጅም ዓመታት መቆየታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የበፊት ብርሀናቸውን ለመለሰላቸው ለጎንደር ዩኒቨርሲቲና ለህክምና ቡድኑ ላቅ ያለ ምስጋና ማቅረባቸውን ቦታው ድረስ በመሄድ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



