የአዲስ ህይወት በጎአድራጎት ማህበር አባላት ነዳያንንና ህሙማንን በመጎብኘትና በመደገፍ የትንሳኤን ሳምንት አሳለፉ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ህይወት በጎአድራጎት ማህበር የተለያዩ በአላትን ከአረጋዊንንና አቅመ ደካሞች ጋር በማሳለፍና ነዳያንን በመደገፍ የተለያዩ መልካም ተግባራትን እንደሚያከናውን ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የማህበር አባላት ከትንሳኤ አስከ ዳግማይ ትንሳኤ ያለውን ሳምንት በሆስፒታል ያሉ ህሙማንን እና በካለን ብናካፍል በጎአድራጎት ማህበር ያሉ ነዳያንን በመጎብኘት የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል፡፡

የአዲስ ህይወት በጎአድራጎት ማህበር የተመሰረተበትን 11ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የማህበሩ አባላት ህሙማንን በመጎብኘት፣ ነዳያንን በማግደፍ ፣የተለያዩ አልባሳትን ከማህበረሰቡ በማሰባሰብና ለነዚህ ወገኖች በመስጠት፣የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ህጻናት የተሟላ የሊስትሮ እቃዎችን በመስጠት ሳምንቱን እንዳሳለፉ የበጎ አድራጎት ማህበሩ ሰብሳቢ ተማሪ በፀጋው ደምሴ ገልጧል፡፡ ሰብሳቢው አክለው እንደገለጹት ለህጻናት የተሰጡት የሊስትሮ እቃዎች ብዛት አስር ሲሆን ይህም ህጻናቱ ሰርተው በኢኮኖሚ የመጠቀም ተነሳሽነት እንዲኖራቸውና ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያሳልፍ ያግዛል፡፡
በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ፈቃድ በስድስት ዶክተሮች ግንቦት 1/2002 ዓ.ም የተመሰረተው የአዲስ ህይወት በጎአድራጎት ማህበር እስከ አሁን ድረስ በርካታ አባላትን በማፍራት ብዙ መልካም ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ወጣት ታመነ ፀጋየ (የአዲስ ህይወት በጎአድራጎት ማህበር አባል) አንስቷል፤አያይዞም ማህበሩ ቋሚ የኢኮኖሚ ምንጭ ስለሌለው ፈቃደኛ የሆነ ሁሉ በአባልነት በመሳተፍና በገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ ወገኖችን ለመርዳት ያግዝ ዘንድ አሳስቧል፡፡
አልባሳቱንና የሊስትሮ እቃዎቹን የተቀበሉት የካለን ብናካፍል በጎ አድራጎት ማህበር ስራአስኪያጅ አቶ ዳዊት አየነው በካለን ብናካፍል ማህበር ውስጥ እስከ 80 የሚሆኑ አረጋዊያን፣አቅመዳካሞችና የአእምሮ ህሙማን ታቅፈው የህዝቡን ድጋፍ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነውና ሰው የሆነ ሁሉ በሚችለው አቅም በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣በአልባሳትና በሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ የበጎ አድራጎት ማህበሩን እንዲረዳ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ማህበሩን መርዳት ለምትፈልጉ ሁሉ፡ የባንክ አካውንት(የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) 1000263359023 ሲሆን
በስልክ ቁጥር 0913227478 /0918828200 ደውላችሁ የማህበሩን አስተባባሪዎች ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
“ካለው አካፍሎ የጎደለው የለም!”




