“የአድዋ ጦርነትን በድል የመወጣት ቁልፍ ሚስጥር ‘አንድነት’ ነው::” ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአድዋ የድል በዓልን በየአመቱ ያከብራል፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓመት የተከበረውን 124ኛውን የአድዋ የድል በዓል የካቲት 25/2012 ዓ.ም በሳይንስ አምባ አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት አክብሯል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የጎንደር አባት አርበኞች አባላት፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት፣ በተለያዩ ትምህርታዊና ኪነ-ጥበባዊ በሆኑ ትዕይንቶችና መሰናዶዎች የድል በዓሉ በድምቀት ተከብሯል፡፡

ዶ/ር አስራት በመክፈቻ ንግግራቸው የአድዋ ጦርነትን በድል የመወጣት ቁልፍ ሚስጥር “አንድነት” መሆኑን በአንክሮ ከተናገሩ በኋላ ወጣቱ በተለይም ሀገርን ለመረከብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪወች የአንድነትን ፋይዳ ከቀደሙ አባቶች በውል በመረዳት፣ የሀገራቸውን ሰላም በማስጠበቅ፣ እራሳቸውን ብሎም ወገናቸውን የማገልገል ሀላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ የአድዋ የድል በዓለን በተመለከተ ለውይት እሚሆን መነሻ ጹሁፍ በሀገር ውጪና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የታሪክ ምሁር በፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ ቀርቧል፡፡ ፕሮፌሰሩ የአድዋ ድል በዓለም ላይ ከተደረጉ ድሎች በላይ የተለየና እሚደነቅ መሆኑን የተለያዩ ታሪካዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህብራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የተለያዩ ትም/ክፍሎች ተማሪዎችና መምህራን አድዋን የሚዘክሩ የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ሙዚቃዊ ተውኔቶችን፣ ቲያትሮችን፣ ሽለላዎችንና ፍከራዎችን በማቅረብ ተሳትፈዋል፡፡ በቀረቡት ዝግጅቶች ታዳሚዎች መደሰታቸውን ለማየት ችለናል፡፡
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



