‘የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ታሪካዊ ዳራ’ በሚል ርዕስ አውደ-ጥናት ተካሄደ
ድንበር/ወሰን የሉዐላዊ ሀገር ክልላዊ መስመር ከመሆኑ ባሻገር የአንድ ሀገር ህዝቦች በዜግነት እሚካተቱባትና ያለ ገደብ የሚንቀሳቀሱበት መስመር ነው፤ ድንበር የአንድ ሀገር መንግስት ህዝቡን በኃላፊነት የሚመራበትና የሚያስተዳድርበት ዓለም አቀፍ መስመር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያና ሱዳን ከ 1600 ኪ.ሜ በላይ የሚጋሩት ወሰን ቢኖራቸውም እስከ አሁን ይህ ነው የሚባልና በህግ ተለይቶ የሚታወቅ የወሰን ክልል ሳይኖራቸው ለረዥም ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በምዕ/ጎንደር ዞን አስተዳደር የጋራ ትብብር የኢትዮ-ሱዳን ደንበር ታሪካዊ ዳራ በሚል ርዕስ ሀምሌ 24/2012 ዓ.ም በዩኒቨርሰቲው ሳይንስ አምባ አዳራሽ አውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር የተከበሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ሎሎች የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመጡ ሙያተኞች፣ ከጎንደርና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ምሁራንና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በአውደ-ጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን ከጥንት ጀምሮ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚአዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳሉአቸው በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ያወሱት ዶ/ር አስራት፣ የሁለቱ ሀገራትን ግኝኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ 6 የሱዳን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትምህርት፣ በህገ- ወጥ ሰዎች ዝውውር፣ በአባይ ጉዳይና በሌሎች መስኮች በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ሀገራቱ አዋሳኝ ድንበሮቻቸውን መሰረት በማድረግ የሚታየውን አለመግባባት በአጭር ጊዜ ለመፍታትና በጋራ እንዲበለጽጉ ለማስቻል፣ ሳይንስና ታሪክን መሰረት ያደረገ በቂ ጥናትና ምርምሮች በዘርፉ ምሁራን መካሄድ እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ አያይዘው አሳስበዋል፡፡ ሀጋራችን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ሰፊ አዋሳኝ ድንበር ያላት ቢሆንም አስከ አሁን የለየ ክለላ ባለመደረጉ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ- አደሮች ለተለያዩ ጉዳቶች ሲዳረጉ መቆየታቸውን የምዕ/ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ችግር በፍጥነት መፍትሄ ያገኝ ዘንድ የአውደ-ጥናቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን በበኩላቸው በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በተደጋጋሚ ከሱዳን መንግስት ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን በሀገራቱ መካከል ያለው የወሰን ክለላ በቶሎ እልባት ባለማግኘቱ የተነሳ ችግር የመፍጠር ፍላጎት ላላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸው መቆየቱን ርዕሰ መስተዳደሩ አያያይዘው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር የአዋሳኝ ድንበር የክለላ ስራ በአጭር ጊዜ መፍትሄ እንዲያገኝ የማድረግም ሆነ በጎንደርና በሱዳን – ገዳሪፍ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት ሰለማዊ የማድርግ ስራ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ተመስገኝ ተናግረዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአለም አቀፍ ህግ ባለሙያ በሆኑት በወ/ሮ ለምለም ፍስሃ – ስለ “ኢትዮ ሱዳን ድንበር የስምምነት ማዕቀፍ”፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበሮች አማካሪ በአቶ ውሂብ ሙሉነህ ደግሞ – ስለ “ኢትጵያ -ሰዳን ድንበር ጉዳይ ታሪካዊ ዳራና ወቅታዊ ሁኔታው”፣ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ በአቶ አለማየሁ እርቅይሁን – “ የጊዌን መስመር ውዝግብና በኢትዮ- ሱዳናዊያን ግንኙነት ላይ ያለው ተፅዕኖ/Controversy over the Gywnn Line & Its effect on Ethio – Sudanese Relations” – በሚሉና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ በሁኑት በፕ/ር ሙላቱ ውብነህ (ውይይቱ ላይ ከአሜሪካ በቴሌ-ኮንፈረንስ በቀጥታ ተሳትፎ ያደረጉ) – “የኢትዮ ሱዳን ወሰን ታሪካዊ ሂደቱና አለመካለሉ ለፈጠራቸው ችግሮች የመፍትሄ ሀሳቦች” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አራት ጥናታዊ ጽሁፎች እንደየ ቅደም ተከተላቸው ቀርበዋል፡፡

የቀረቡትን ጥናታዊ ጽሁፎች መሰረት በማድረግ ከክቡር ርዕሰ መስተዳድሩና ከአማራ ክልል ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ ከአቶ አገኘሁ ተሻገር ጋር ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት አድርገውባቸዋል፡፡ ለወደፊት ይበጃሉ የተባሉ ምክረ ሀሳቦችም ተጠቁመው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬትሐምሌ
24/2012 ዓ.ም



