“ የእናቶች እናት”-ዶ/ር አምባዪ ወ/ሚካኤል የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አገኘች

ከኢትዮጵያም ሆነ ከኣፍሪካ አልፎ በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ የማህፀንና ፅንስ ቀዶ ጥገና ሀኪሞች ዉስጥ አንዷ እንደሆነች ተመስክሮላታል። ህይወቷን ለሙያዋ አሳልፋ የሰጠች ዉድ ኢትዮጵያዊት ስትሆን በተለይም በሴት እህቶቻችንና እናቶቻችን ላይ በስፋት ችግር ኣያደረሰ ባለዉ የፊስቱላ ህመም ላይ የቀዶ ጥገና ሕክምና በማድረግ ከ20 ዓመታት በላይ በሽዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ብሎም አፍሪካዉያን ሴቶችና እናቶችን ከሞት የታደገች፣ እምባ ያበሰችና፣የጨለመ ተሰፋቸዉን ያበራች አንጋፋ ምሁርነች- ዶ/ር አምባዪ ወ/ሚካኤል ። ለዚህም የስራ ባልደረቦችዋ “ የእናቶች እናት” ወይም (“ Mother of Mothers” ) የሚል ስያሜ ሰጥተዋታል፡፡

እ.ኤ.አ. ግንቦት 14 ቀን 1963 አዲስ አበባ ዉስጥ ነዉ የተወለደችዉ። ለቤተሰቦቿ ስምንተኛ ልጅ ስትሆን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃት ምህርቷን ያጠናቀቀችዉ እዛዉ አዲስ አበባ ነዉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ምስራቅ አጠ/2ኛ/ደ/ት/ቤት እንዳጠናቀቀች የአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲን የህክምና ፋኩልቲ በመቀላቀል እ.ኤ.አ. በ1984 በህክምናዉ ዘርፍ የመጀመሪያ ሜዲካል ዶክትሬቷን አግኝታለች።
የመጀመሪያ ሜዲካል ዶክተሬት ዲግሪዋን ካገኘች በኋላም በጋምቤላና የካቲት 12 ሆስፒታሎች በአጠቃላይ ሀኪምነት ያገለገለች ሲሆን በተለይም ጋምቤላ ሆስፒታል ላይ ትሰራ በነበረችበት ወቅት በብዙ ሴቶች ላይ ያስተዋለችዉ የፊስቱላ ህመም ስቃይ ነበር የወደፊት የሙያ አቅጣጫዋን እንድትወስን መነሳሳትና ተጽእኖ የፈጠረባት።በመሆኑም እ.ኤ.አ. በ1986 እንደገና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመለስ የማስትሬት ዲግሪዋን በማህፀንና ፅንስ የህክምና ዘርፍ ካገኘች በኋላ በተለያዩ ተቋማት በከፍተኛ ሙያዊና የሀላፊነት እርከኖች ላይ ለሀገሯ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
ይኸዉም፡-
- እ.ኤ.አ. ከ1992-1997 በማህፀንና ፅነስ ቀዶ ጥገና ሀኪምነት
- ከ1998-1999 እ.ኤ.አ. በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል በረዳት ሜዲካል ዳይሬክተርነት፣ በመቀጠልም በዚሁ ሆስፒታል ዉስጥ በሜዲካል ዳይሬክተርነት፣ በአማካሪነት፣ በዋና ፊስቱላ ቀዶ ጥገና ሀኪምነትና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር በመሆን እስከ 2008 እ.ኤ.አ. ያገለገለች ሲሆን በእነዚህ አመታት ዉስጥ ብቻ ዶ/ር አምባየ ከ5000 በላይ የፊስቱላ ህመምተኞችን የቀዶ ጥገና ሕክምና በመስጠት ሕይወታቸዉንና፣የጨለመ ተሰፋቸዉን እንደገና አለምልማለች።
በመቀጠልም በ2006 እ.ኤ.አ በእንግሊዝ ሀገር በሚገኘዉ University of Leeds, International school of Public Health ትምህርቷን በመከታተል በጤና አጠባበቅ ዘርፍ(public Health) ተጨማሪ የማስትሬት ዲግሪዋን አግኝታለች።
ዶ/ር አምባዪ በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ዉስጥ ብቻ ተወስኖ የቆየዉ ሕክምና ተደራሽ እንዲሆንና በሌሎች አምስት የክልል ከተሞች ማለትም በባህርዳር ፣ መቀሌ፣ ይርጋለም፣መቱና ሀረር ላይ የፊስቱላ ማዕከላት እንዲፈጠሩ ከፍተኛዉን ድርሻ ያበረከተች ዉድ የኢትዮጵያዉያን ባለዉለታ ነች።
ከኢትዮጵያም አልፎ ዶ/ር አምባዪ በተለያዩ የአፍሪካና ሩቅ ምስራቅ አገሮች በፊስቱላ ህመም ይሰቃዩ ለነበሩ ህሙማን ብርሀን የሆነችና በእነዚህ ሀገራት ቀጣይነት ያለዉ ሕክምና እንዲኖር በታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ኬኒያ፣ሞዛምቢክ፣ ዲሞክራቲክ ረፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊላንድ፣ ዝምባብዌ፣ አፍጋኒስታን ስልጠና በመስጠትና ሰር-ዓተ ትምህርት በመቅረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተችና በአለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈች አንጋፋና ዉድ የአፍሪካ ልጅ ነች።

ዶ/ር አምባዬ በዘርፉ በርካታ ምርመሮችን በመስራት ለህትመት ያበቃች ሲሆን የተለያዩ መሀፎችንም አሳትማለች፡፡
ዶ/ር አምባዬ ለሀገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን እንደ AMREF Kenyatta Hospital, UNFPA MALI, እና Engender health Rwanda ለሚባሉና ሌሎችም አለም አቀፋዊ ተቋማት የማማከር አገልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡
እ.ኤ.አ. ከ 2009 ጀምሮ የፊስቱላ ቀዶ ጥገና ህክምና አስተባባሪ ሀኪምና አሰልጣኝ በመሆን WAHA (women and Health Alliance) በተሰኘዉና ከዩኒቨርሲቲያችን ጋር በአጋርነት እየሰራ በሚገኘዉ አለም አቀፋዊ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዉስጥ በማገልገል ላይ ትገኛለች።ዶ/ር አምባዬ ያበረከተችዉን አስተዋጽኦ በዚህ አጭር ጊዜ ዉስጥ ዘርዝሮ መጨረስ ባይቻልም የጎንደር የዩኒቨርሲቲ ሴኔት ያበረከተችዉን አስተዋፅኦ በዝርዝር ከገመገመ በኋላ የክብር ዶክትሬት አንዲሰጣት ወስኗል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዚህች የስራዋን ያህል ላልተዜመላት አንጋፋ ምሁርና የብዙ ኢትዮጵያዊያን ባለዉለታ የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ ከፍተኛ ከብር ይሰማዋል፡፡
በኤልያስ መንበረ
የአለም አቀፍ ግንኙነት ም/ዳይሬክተር
phone-0918079577
E-mail: eladetelias@yahoo.com



