የእንስሳት ሀብት አጠቃቀም ስርዓትን ከምግብ ዋስትና እና ከዝቅተኛ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀት ጋር ማጣጣም ላይ ትኩረት ያደረገ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደ ጥናት ተካሄደ
UNIQUE Land use ከILRI ፣ AICCRA ፣ FANRPAN እና ACIAR ጋር በመተባበር በደቡብ እና ምስራቅ አፍሪካ መጠነ-ሰፊ የእንስሳት ሀብት ስርዓትን በማላመድ ለምግብ እና ስነ-ምግብ ዋስትና እንዲሁም ለዝቅተኛ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀት መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረገ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደጥናት ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል (አዲስ
አበባ )ተካሔደ።
በአውደ ጥናቱ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላት ጥሪ የተደረገላቸው ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ በእንስሳት እርባታ እና በዘር ማዳቀል ተግባር ላይ ሰፊ ልምድና እውቀት ያካበቱ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብትና እርባታ ሥርዓት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ጥናቶች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የምርምር ልምድ እንዳላት የ”UNIQUE Land use” (መሰረቱን ጀርመን ሀገር ያደረገ አለምአቀፍ አማካሪ ድርጅት) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ቲም ቴኒንግኬይት ተናግረዋል።
ስለሆነም አዲስ የተጀመረው ፕሮጀክት የእንስሳት ሀብት አጠቃቀምን በማዘመንና በማላመድ የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተሳታፊ የሆኑ ሀገራትን እንደሚጠቅም ጠቁመዋል።
ስለታዳጊ እንስሳት ሞት፣ ስለእንስሳት ጤና መጓደል ፣
ከማህበረሰብ አቀፍ የእንስሳት እርባታ ጋር ስለተያያዙ ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም ስለእንስሳት እርባታ ፣ የምግብ ዋስትና እና የግሪን ሀውስ ጋዝ ትስስር ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ፅሁፎች በተለያዩ ምሁራን በአውደ ጥናቱ ቀርበዋል፤ በገለፃዎቹ ላይም ውይይት ተካሂዷል።
ዶ/ር ሽመልስ ዋሴ (ከUNIQUE Land use ካምፓኒ) እንደገለፁት አዲሱ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በእንስሳት እርባታ ስርዓት ማጣጣም፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በምግብ ዋስትና ላይ ከዚህ በፊት በተለያዩ የምርምር ፕሮጀክቶች የተሰሩ ተግባራትና ግኝቶች ያመጡትን ለውጥ እና ሶስቱ ሀሳቦች ያላቸውን ትስስር መመርመር ላይ አላማ አድርጎ ስለሚሰራ ፕሮግራሙን የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
“ጎንደር ዩኒቨርሲቲን እንደ አጋር ማካተት ለፕሮጀክቱ ጠቃሚ እሴትን ይጨምራል ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲው በእንስሳት እርባታ፣በእንስሳት ጤና እና በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ብዙ ሰርቷል”ሲሉም አክለዋል።
የእንስሳት እርባታ ለሀገራችን ወሳኝ ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያመጣው ከፍተኛ ተፅዕኖ ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ መሆኑን በጥናታቸው አንስተዋል።
አንዳንድ እንስሳት “ሚቴን” ጋዝን በእበት፣በሽንት ወይም በአተነፋፈስ ጊዜ ይለቃሉ እና ይህ ጋዝ የ GHG ልቀትን ያስከትላል ሲሉም ዶ/ር ሽመልስ ዋሴ አብራርተዋል።
ከእንስሳት የሚወጣው ይህ ጋዝ ጉልበት ነው።ስለሆነም
እንስሳቱ ይህን ጉልበት እንዲጠቀሙ እና የስጋ እና የወተት ተዋጽኦዎችን በከፍተኛ እንዲያስገኙ ማድረግ ይቻላል ሲሉም ጠቁመዋል።ይህም የእንስሳት ምርቶችን ለመጨመርና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያለውን የግሪን ሀውስ ጋዝ ተፅእኖ ለመቀነስ እንደሚረዳ ተገልጿል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ፀጋው ፈንቴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ 50% ገደማ የሚሆነው ታዳጊ እንስሳት ለሞት እንደሚጋለጥ ባቀረቡት ጥናት አንስተዋል። ለዚህም ምክንያቶቹ ከበሽታ፣ ከአስፈላጊ መኖ እጥረት፣ ከእንስሳት አያያዝ ጉድለት እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀዋል ። ስለሆነም እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ የታዳጊ እንስሳትን ሞት መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከፕሮጀክቱ ጋር በመተባበር በአቅም ግንባታ ፣በድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች እና በምርምሮች ላይ የተሻለ ስራ ለመስራት መልካም እድል እንደሚፈጥር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና እና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሽመልስ ዳኛቸው ገልፀዋል።
በመጨረሻም በፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ በድህረ ምረቃ ተማሪዎች የሚካሄዱ የምርምር ርዕሶችን ቅድሚያ ሰጥቶ ለመምረጥ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በዚህምጨመሠረት ማህበረሰብ አቀፍ የእንስሳት እርባታ እና የእንስሳት ጤና የምርምር ዘርፍ ተደርገው ተመርጧል።