የካንሰር ታካሚዎች ህፃናት ማቆያ ማዕከል በጎንደር ከተማ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ተገለፀ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠ/ስፔ/ሆስፒታል ከተስፋ አዲስ የህጻናት ካንሰር ህክምና በጎአድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር የካንሰር ታማሚ ህጻናት አስፈላጊውን የህክምና ፣የስነልቦና፣ የመጠለያና የምግብ አገልግሎት እያገኙ የሚቆዩበት ማቆያ ማዕከል በጎንደር አዘዞ መገንጠያ አካባቢ በዚህ አመት ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠ/ስፔ/ሆስፒታል የህክምና ት/ቤት ኃላፊና የህፃናት የደምና የካንሰር ስፔሻሊስት ዶ/ር ሙሉጌታ አያሌው ገልጸዋል፡፡

“የህጻናት ካንሰር አይነቱ ቀድሞ ከታወቀ በህክምና የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው፣” ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ ይህ የሚሆነውም ሙሉውን የህክምና ሂደት በአግባቡ ሲከታተሉ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ሆስፒታሉ በክልሉ ብቸኛ የህጻናት የደምና የካንሰር ህክምና ማዕከል መሆኑን የገለጹት ስፔሻሊስቱ ፣የህጻናት ካንሰር ህክምና በጤና ባለሙያ፣ በደምና በመድሀኒት አቅርቦት፣በማህበራዊና ስነ ልቦናዊ አገልግሎት ረገድ በርካታ ግብአቶችን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ እንደካንሰሩ አይነት ህክምናው ከስድሰት ወር እስከ ሁለት አመት ተኩል ገደማ ሊወሰድ ስለሚችል በተደጋጋሚ ወደ ህክምና ማዕከል መመላለስን ይጠይቃል፣ ያሉት ዶ/ር ሙሉጌታ ይህ የህክምና ሂደት በቤተሰብ ላይ የኢኮኖሚና የማህበራዊ -ስነ ልቦናዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ወላጆች የካንሰር ታማሚ ልጆቻቸውን ህክምና መከታል ሲያቅታቸው ህክምናውን እንደሚያቋርጡ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ዩኒቨርሰቲ ሆስፒታሉ ከተስፋ አዲስ የህጻናት ካንሰር ህክምና በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር የካንሰር ታማሚ ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን አስፈላጊውን የህክምና ፣የስነልቦና፣ የመጠለያና የምግብ አገልግሎት የሚያገኙበት ማቆያ ማዕከል በጎንደር አዘዞ መገንጠያ አካባቢ በዚህ አመት መከፈቱን ስፔሻሊስቱ ገልጸዋል፤ የህጻናቱን እድሜ መሰረት ያደረገ የስነ ልቦና ድጋፍ ለመስጠትም ከተስፋ አዲስ በጎ አድራጎት ማህበርና ከዩኒቨርሲቲው የስነ ልቦና ባለሙያ ተመድቦ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ዶ/ር ሙሉጌታ አያይዘውም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታካሚ ቢኖርም ማቆያ ማዕከሉ በአንዴ ማስተናገድ የሚችለው ከስምንት እስከ አስር ሰው ብቻ መሆኑን ገልጸዋል ፤ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣የከተማው ባለሀብትና መላው የአከባቢው ማህበረሰብ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ በማድረግና የልጆችን ህይወት በመታደግ እንዲሳተፍም አሳስበዋል፡፡




