የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽ በሽታን ለመከላከል የተቋቋመው አብይ ግብረ ሀይል የተከናወኑ ተግባራትን ገመገመ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽ በሽታን ለመከላከል አንድ አብይ ግብረ ሀይል እና በየግቢው ንዑስ የኮሮና ቫይረስ ክትትልና ቁጥጥር ኮሚቴ በማዋቀር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

አብይ ግብረ ሀይሉ መጋቢት 8/2012 ዓ.ም ባደረገው ውይይት ለእያንዳንዱ ንዑስ ግብረ ሀይል ተግባራትን ቆጥሮ በመስጠት የየበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት መጋቢት 11/2012 ዓ.ም አብይ ግብረ ሀይሉ በሴኔት አዳራሽ በመሰብሰብ በየግቢው የተከናወኑ ተግባራትን ገምግሟል፡፡

በግምገማው ከተማሪዎች አገልግሎት፣ ከፋይናንስና በጀት፣ ከግዥና ንብረት አስተዳደር፣ ከኮምዩኒኬሽን እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ አንፃር የተከናወኑ የቅድመ መከላከል ስራዎችን በማንሳት ተወያይቷል፡፡ በውይይቱ በቅድመ መከላከል ስራዎች ላይ ያጋጠሙ ችግሮችንና የተወሰዱ መፍትሄዎችን በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በዚህም መሰረት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና ተማሪዎች ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ የውሀ አቅርቦት ችግር ሲያጋጥም ውሀ በቦቲ በማስመጣት ችግሩ እንዲፈታ፣ በተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ ውስጥ ያሉ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ተራርቀው እንዲቀመጡ እና በአንድ የመመገቢያ ጠረጴዛ አራት ተማሪዎች ብቻ እንዲጠቀሙ እንዲሁም ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ህሙማንን ለመጠየቅ የሚመጡ ግለሰቦች መጨናነቅ እንዳይፈጥር እየተሰራ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ለአንድ ህመምተኛ አንድ አስታማሚ ብቻ እንዲፈቀድ የሚሉ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት



