
የኽልት ሽልማት ፋውንዴሽን ( Hult Prize Foundation 2023) የ2015 ዓ/ም የስልጠና መክፈቻ መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኽልት ሽልማት ፋውንዴሽን ( Hult Prize Foundation 2023) የስራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የ2015ዓ/ም የስልጠና መክፈቻ መርሃ ግብር የካቲት 6/2015ዓ/ም በማራኪ አልሙኒዬም ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፡፡

በዚህ መርሃ ግብር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዉጤታማ ሥራ አተገባበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አራጋው እሸቴ፣ በዉጤታማ ሥራ አተገባበር ክፍል ባለሙያና የሞያ ማጎልበቻ ማዕከል አስተባባሪ መ/ር አሸናፊ ደሳለኝ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኽልት ሽልማት ፋውንዴሽን መስራችና ባለፉት ዓመታት በካምፓስ ዳይሬክተርነት ያገለገለችው ወ/ሪት እድላዊት አሻግሬ፣ የኽልት ሽልማት ፋውንዴሽን የካምፓስ ዳይሬክተር ተማሪ በፍቃዱ ብርሃኑ፣ ም/ዳይሬክተሯ በእምነት ኢሳያስ፣ የስራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ተማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

ኸልት ሽልማት ፋውንዴሽን ከዓለም ትልቁ የማህበራዊ ስራ ፈጠራ ውድድር አንዱን ያቋቋመ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። የኸልት ሽልማት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር ወጣቶች በተፅዕኖ በተደገፉ ፕሮግራሞች ይለውጣል። የኸልት ሽልማት በአሜሪካ ውስጥ በተካሄደው የፍጻሜ ውድድር ላይ የሚሰጠውን የ1ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሀሳብ ለማውጣት ከኮሌጆች/የዩኒቨርስቲ ከተማሪዎች ሀሳቦችን ያሰባስባል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኽልት ሽልማት ፋውንዴሽን መስራችና ባለፉት ዓመታት በካምፓስ ዳይሬክተርነት ያገለገለችው ወ/ሪት እድላዊት አሻግሬና የኽልት ሽልማት ፋውንዴሽን የካምፓስ ዳይሬክተር ተማሪ በፍቃዱ ብርሃኑ መርሃ ግብሩን አስመልክቶ ቁልፍ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የዉጤታማ ሥራ አተገባበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አራጋው እሸቴ ደግሞ በቀጣዮቹ የስልጠናና የውድድር ጊዚያት ተማሪዎቹ ሊያተኩሩባቸው በሚገቡ ነጥቦች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ፣ ሀገር አቀፍና በሥነ-ምግባርና በክህሎት የታገዙ ምሁራንን ማፍራት፣ እነዚህ ምሁራን ደግሞ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው የሀገርን ችግር የሚፈቱ፣ በዓለም ደረጃም አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ስራ ፈጣሪዎችና የስራ ባለቤቶችን ማግኘት ዋነኛው ዓላማ እንደሆነ ዶ/ር አራጋው አክለው ተናግረዋል፡፡

በመቀጠል በዩኒቨርሲቲው የሞያ ማጎልበቻ ማዕከል አስተባባሪና በሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መ/ር በሆኑት በአቶ አሸናፊ ደሳለኝ በመሰረታዊ የህይወት ክህሎት፣ በስራ ፈጠራና በኽልት ሽልማት የስራ ፈጠራ ውድድር ሂደት አጋዥ በሆኑ ርዕሶች ላይ ስለጠና ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በቀጣይ ስራዎችና በሚካሄዱ መርሃግብሮች ዙሪያ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡



