
የወገራ ወረዳ በመረጃ አብዮት (በጤና መረጃ አያያዝ ስርዓት) ወደ ሞዴል ወረዳ ተሸጋገረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ የጤና ስርዓትን ለማጠናከር የአቅም ግንባታና ድጋፍ በማድረግ በአማራና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተመረጡ ወረዳዎች ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ከሚሰራባቸው ወረዳዎች መካከል አንዱ የሆነው የወገራ ወረዳ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ተለክቶ ሚኒስቴሩ ያስቀመጠውን የትራንስፎርሜሽን መለኪያ በማሟላቱ ወረዳው ሞዴል ወረዳ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

ሞዴል ወረዳ መሆኑን አስመልክቶ በሰኔ 26/2013 ዓ.ም በዐምባ ጊወርጊስ ከተማ በተዘጋጀው መርሀ-ግብር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶ/ር አስማማው አጥናፉ፣ የጤና ሚኒስቴር የእቅድና ክትትል ምክትል ዳሬክተር የሆኑት አቶ መሱድ ሙሀመድ፣ የማእከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገቢያው አሻግሬ፣ የፕሮጀክቱ አባል መምህራንና ተመራማሪዎች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የጤና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ የጤና ሚኒስቴር የእቅድና ክትትል ምክትል ዳሬክተር የሆኑት አቶ መሱድ ሙሀመድ የተሰራውን ስራ አድንቀው በተመሳሳይ ሌሎች ወረዳዎች ላይም እንዲስፋፋ መክረዋል፡፡ የማእከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገቢያው አሻግሬ በበኩላቸው ወገራ ወረዳ ላይ የተሰራውን ስራ ወደ ሌሎች የዞኑ ወረዳዎች ለማስፋፋት ወደፊት ከዩኒቨርሲቲውና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ወገራ ወረዳ ሞዴል በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በቀጣይ ወረዳውን የቴክኖሎጅ ሽግግር ማሳያ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴርና ፕሮጀክቱን ከሚደግፈው DDCF ጋር በትብብር የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
