የውሻ ንክሻን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ የውሻ ንክሻን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል በንድፈ-ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና ለእንስሳት ህክምና ሙያተኞችና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ዛሬ የካቲት 13/2013 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡

የጎንደርዩ ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምናና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሽመልስ ዳኛቸው፣ የዩኒቨርሲቲው ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው መኩሪያ፣ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የእንስሳት ህክምና ሙያተኞችና ባለሙያዎች በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡

የእብድ ውሻ በሽታ (rabies) አስከፊ ከሚባሉ የሰውና የእንስሳት በሽታዎች በግንባር ቀደም ይጠቀሳል፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ስለ እብድ ውሻ በሽታ በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ እንዳለ ሁኖ ባለቤት አልባ የጎዳና ውሻዎች በብዛት በየቦታው መኖራቸው ደግሞ ለበሽታው መዛመት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በእብድ ውሻ በሽታ ምክንያት የበርካታ ሰዎችን ህይዎት በማጣት ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መረጃዎች ያመለክተሉ፡፡

በመሆኑም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ምሁራን ከውሻ ጋር ቀረቤታ ያላቸውም ሆነ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በውሻዎች እንዳይነከሱ የሚረዱ እና በተጓዳኝ ከውሻ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስቸሉ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ለማስገንዘብ ዓላማ ያደረገ ስልጠና እንደሰጡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡



