“የዩኒቨርሲዎቻችን አሁናዊ ተግዳሮት” መጽሐፍ በታላቅ ድምቀት ተመረቀ
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ ደራሲነት የተዘጋጀው “የዩኒቨርሲዎቻችን አሁናዊ ተግዳሮት” የተሰኘ መጽሐፍ በታላቅ ድምቀት ተመርቋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በማራኪ ግቢ አልሙኒየም አዳራሽ የተካሄደው የምርቃት መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ አመራሮችና መምህራን በታዳሚነት ተገኝተዋል፡፡
መፅሐፉን ከቋንቋና ስነ ፅሁፍ ውበቱ አንፃር ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ (የማህበራዊና ሥነ ሰብዕ ኮሌጅ ዲን) የተነተኑት ሲሆን ከይዘትና ነባራዊ አውዱ አኳያ ዶ/ር እንዳልካቸው ተሾመ ቀኝተውታል፡፡ በመጽሐፉ ላይ ታዳሚዎችም ገንቢ አስተያየቶችን ሰጥተውበታል፡፡

በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመጽሐፉ ደራሲ ዶ/ር ታፈረ መላኩ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ላሳያቸው ክብር አመሰግነው፣ እንዴት እንደፃፉት ገለፃ አድርገዋል፡፡ እንዲሁም ከችግሮች ተምሮ የተሻለ ነገ እንዲመጣ ከመመኘት የመነጨ ተነሳሽነት ለመፃፍ እንዳነሳሳቸው ጠቅሰዋል፡፡

በመጨረሻም “የዩኒቨርሲዎቻችን አሁናዊ ተግዳሮት” መፅሐፉን ለሚፈልጉ አንባቢያን ሽያጭ ላይ መሆኑን እንገልፃለን፡፡



