የጆርናል ግምገማና የእውቅና መስጠት መርሐ ግብር ተካሄደ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ Ethiopian Renaissance Journal of Social Science and Humanities (ERJSSH) የተሰኘውን የኮሌጁን ጆርናል ሂደት ግምገማ መርሃ- ግብር ሚያዚያ 15/2013ዓ/ም በማራኪ አልሙኒዬም ህንፃ አዳራሽ አካሂዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ምርጥ ተማሪዎች፣ ምርጥ መምህራን፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ለጆርናሉ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች የምስጋናና የዕውቅና መስጠት ስነ-ስርአት ተከናውኗል፡፡

በፕሮግራሙ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ፣ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተገኝተዋል፡፡
ጠንካራ ስራዎች የሚሰሩት ለተሰሩ ስራዎች እውቅና መስጠት ሲቻል እንደሆነ በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግራቸው የገለፁት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጨቅሉ ፣ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ጠንካራ ስራ ለሰሩ ተማሪዎች መምህራንና ተመራማሪዎች የእውቅና ፕሮግራም በማዘጋጀት እውቅና መስጠቱን አድንቀዋል፡፡ ዶ/ር ቢኒያም አያይዘውም ጆርናሉን ከምስረታው ጀምሮ ሲሰሩ የቆዩትንና አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያበቁትን በየደረጃው ላሉ አካላት ያላቸውን አድናቆት ገልፀው፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት ስም አመስግነዋል፡፡

በመቀጠል የጆርናሉን አመሰራረትና እስካሁን ያለው ሂደት በዶ/ር ቡሻ ተዓ የውይይት መነሻ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የላቀ ውጤት ላመጡ ስድስት የኮሌጁ ተማሪዎች፣ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ ተመራማሪ፣ መምህር፣ ለጆርናሉ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ዶ/ር ቡሻ ተዓን ጨምሮ ለሌሎች ምሁራን የምስክር ወረቀትነና እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
በመጨረሻም በአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ የፕሮግራሙ መዝጊያ ንግግርና የስራ አቅጣጫ የሰጡ ሲሆን፣ ጆርናሉን ከምስረታው ጀምረው ከዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላበረከቱ ምሁራን ያላቸውን አክብሮት ገልፀው ወደፊት በሌሎች ኮሌጆችም እውቅናን መስጠት ሊለመድ የሚገባው አሰራር እንደሆነ አበክረው ተናግረዋል፡፡




