የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአዕምሮ ህክምና አገልግሎት
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የስነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎችን ከሀይማኖት አባቶች ጋር በማቀናጀት በአብዛኛው ለሚከሰቱ የአዕምሮ ህመምና ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ የስነ-ልቦና ችግሮች በአዕምሮ ህክምና አገልግሎት ላይ ከህዳር 29-30/2013 ዓ/ም በአምባ ጊዮርጊስ ከተማ በተለያዩ ሁለት አዳራሾች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የስልጠናው አላማ የአዕምሮ ህመም ሁሉም ቦታዎች ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑንና አገልግሎት ሰጪዎችም በጣም አነስተኛ በመሆናቸው ባለሙያዎችን የስራ ላይ ስልጠና በመስጠት፣ አቅማቸውን በማዳበር ህክምናውን እንዲሰጡ ማድረግና ከባለሙያዎቹ አቅም በላይ የሆነ ችግር ሲገጥም ደግሞ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈር ማድረግ የሚችሉበትን አቅም መፍጠር የሚያስችል የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና እንደሆነ የትምህርት ክፍሉ መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አለሙ ለማ በስልጠናው ላይ ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል መምህራን ይህንን ስልጠና መስጠታቸውን በጣም ወቅታዊና ተገቢ ነው ሲሉ የአምባ ጊዮርጊስ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሚካኤሌ ተገኘን ጨምሮ ሌሎች የስልጠናው ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ ተከታታይነት ባለው መልኩ ድጋፍ ቢያደርግ በስራቸው ላሉ ሌሎች ባለሙያዎች አቅም መፍጠር እንደሚያስችል በሥልጠናው ላይ ተጠቁሟል፡፡
የሀይማኖት አባቶች የአዕምሮ ህመምተኞችን በፀበል ቦታዎች እንዴት በመንፈሳዊ መንገድ መርዳት እንደሚችሉ ስልጠናው ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው የተናገሩት መላከ ሰላም ቀሲስ ፈንታሁን ማስረሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በመለየትና በመረዳት ችግሮችን እየፈታ እንደሆነ በመግለፅ ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የተሰጠውን ስልጠና በስብከተ ወንጌሉ ላይ በማካተት ትምህርት በመስጠት የአዕምሮ ህመምተኞችን ለመንከባከብና ለመርዳት እንዲሁም ዘመናዊ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ደግሞ አገልግሎቱን ወደ ሚያገኙበት ተቋም እንዲሄዱ የምክክር አገልግሎት እንደሚሰጡ ያላቸውን ቁርጠኝት ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የወገራ ወረዳ የጤና ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ገነቱ ደጉ የመዝጊያ ንግግር በማድረግ፣ ለሰልጣኞቹ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡ ****************************************************
ሀገራችንን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል!
የህዝብና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ህዳር 30/2013 ዓ.ም







