የጎርጎራ ከተማ መሪ ዕቅድ ዝግጅትን በተመለከተ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የጎርጎራ ከተማ መሪ ዕቅድን የተመለከተ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዚያ 8 እና 9/2013 ዓ.ም በጎሀ ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፡፡
በምክክር መድረኩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ግርማ፣ የአማራ ክልል የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ፀሀፊ ዶ/ር አስማረ ደጀን፣ የቀድሞው የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር መሀሪ ታደሰ፣ የቀድሞው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢ/ር ማስተዋል ስዩም እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ፣ የክልልና የዞን አመራሮችና ባሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የጎርጎራ ከተማ በገበታ ለሀገር ከተመረጠችበት ጊዜ ጀምሮ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነና በተለይም ከተማዋን የሚመጥን፣ ነገን ያማከለ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ዕሴቶችን ማዕከል ያደረገ መዋቅራዊ እቅድ በማዘጋጀት ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

የጎርጎራ ከተማ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ተጠቃሚ በመሆኗና የክልሉ መንግስት የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን ዩኒቨርሲቲው እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት በመሰጠቱ ትልቅ ኩራትና ደስታ እንደሚሰማቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በመክፈቻ ንግግራቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በቀጣይ 3 አመታት 300 ለሚሆኑ የጎርጎራና አካባቢው ወጣቶችን የተለያዩ አጫጭር የሙያ መስክ ስልጠናዎችን በመስጠት ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ዩኒቨርሲቲው ከምዕ/ደንቢያ አስተዳዳር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፤በተጨማሪም በጎርጎራ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለሚያበረክቱ አስራ አምስት ታታሪ ባለሙያዎች ነፃ የመጀመሪያና የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ለመስጠትና ሌሎች ስምምነቶችም በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና በወረዳው አስተዳዳሪ ተፈጽመዋል፡፡

በዚህ ሀገራዊ የውይይት መድረክ የከተማ መሪ እቅድ ከኢኮኖሚያዊና ከማህበራዊ ጉዳይ እይታ አንጻር ምን መምሰል እንዳለበት፣ የውጭ ሀገራት የቱሪስት መስህብ ከተሞች እና የሀገር ውስጥ ከተሞች ልምድ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና የጎርጎራ ከተማ መሪ ዕቅድ ዝግጅትን በተመለከተ በመስኩ ሰፊ ልምድ ባካበቱ ምሁራን የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ውይይቱን ተከትሎም የጎርጎራ ከተማና አካባቢው ጉብኝት ተካሂዶ በፕሮጀክቱ ላይ ለተሳተፉ አቅራቢዎች በዩኒቨርሲቲያችን ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡



