የጎንደር ከ/አስተዳደር አልማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ200 ሺ ብር ቁሳቁስ ድጋፍ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል አበረከተ
የጎንደር ከ/አስተዳደር አልማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለተቋቋመው አዲስ የኮቪድ-19 ህክምና መስጫ ማዕከል የ200 ሺ ብር ቁሳቁስ ድጋፍ ሚያዚያ 17/2012 ዓ.ም አበርክቷል፡፡ የተበረከተው ቁሳቁስ የውኃ ማሞቂያና ማቀዝቀዣ፣ፎጣ፣ጠረጴዛና የግድግዳ ሰዓት የሚያካትት ሲሆን በርክክብ ስነ ስርዓቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የጎንደር ከ/ አስተዳደር ም/ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲውና የከተማው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

“የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እንደ ከተማ አስተዳደርና እንደ ክልል የተለያዩ ተግባራት ስንፈጽም ቆይተናል፣” ያሉት የጎንደር ከተማ አስ/ ም/ከንቲባ ኢንጂነር በሪሁን ካሳሁን፣ ከዚህ ባለፈ ምናልባት በሽታው በአካባቢያችን ቢከሰት ባለን አቅም የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር የኮሮና ህክምና ማዕከል መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ም/ከንቲባው፣ በሽታውን ለመከላከልና ህክምናውን በአግባቡ ለመስጠት የማዕከሉን ግብአት ማሟለት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበው ፣ ከአልማ የተበረከተው የቁሳቁስ ድጋፍም የዚህ አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ኢንጂነር በሪሁን አያይዘውም ህብረተሰቡን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመታደግ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሰል ድጋፍን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ኮቪድ 19 በአለምአቀፍ ደረጃ እደረሰ ያለው ሁለንተናዊ ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፤ይህ ተፅእኖ ደግሞ በታዳጊ ሀገሮች የከፋ ነው፣” በማለት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን በርክክቡ ላይ ተናግረዋል ፡፡ ስለሆነም እየታየ ያለው ትብብር መልካም ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ “አልማ የሁልጊዜ አጋራችን ቢሆንም የዛሬው ድጋፍ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ባለንበት ወቅት በመድረሱ ልዩና ታሪክም የማይረሳው አስተዋጽኦ ነው ፣”ሲሉም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡ የጤና ባለሙያዎቻቸንን ደህንነት ለመጠበቅ “ጎ ፈንድ ሚ” የድጋፍ ማሰባሰቢያ መቋቋሙን የገለጹት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ፤በዚህ አጋጣሚ ለመላው የአለም ህዝብ ድጋፍ እንዲያደርጉና ህዝቡን ከወረርሽኙ እንዲታደጉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ከፉን ያርቅ እንጅ የሰፋ ችግር ቢከሰት እንኳን ከወረርሽኙ ጋር የሚመጣውን ችግር ለመቋቋም ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህ/ጤ/ሳይንስ ኮሌጅና አጠ/ስፔ/ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ ከአልማ በተጨማሪ ከመንገድና ከሆቴል አገልግሎት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት ላደረገው አስተዋጽኦ የከተማ አስተዳደሩን አመስግነዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው አያይዘውም “የህክምና አገልግሎቱን የሚሰጡ የህክምናና የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን ለይተው የሚቆዩበት የሆቴል አገልግሎት ጎሃ ሆቴል ፣ሙሉ የምግብ ወጩን ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፍኑ ቃል ስለገቡ ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፣” ብለዋል፡፡ እየተደረገ ያለው ርብርብ ወረርሽኙን በመመከት ህዝባችንን ለማዳን ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ከወቅታዊ ችግሩ ጋር በተያያዘ በሶስቱ ዞኖችና በከተማ አስተዳደሩ 3.2 ሚሊየን ብር በመመደብ የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና፣ ኮንቲነሮች እና ሌሎች ቁሳቁሶች መሰራጨታቸውን የጎንደር ከ/አስ/አልማ ተወካይ አቶ አለኸኝ ጓዴ ቁሳቁሱን ሲያስረክቡ ገልጸዋል፡፡ በዛሬው እለት ለዩኒቨረሲቲው የኮሮና ህክምና መስጫ ማዕከል የተበረከተው ቁሳቁስ በተመለከተም በአጠቃላይ 200 ሺ ብር የሚያወጡ፣ 10 የውኃ ማሞቂያና ማቀዝቀዣ ፣ 362 የሚሆን ፎጣ፣10 የግድግዳ ሰዓት፣ጠረጴዛና መደርደሪያዎችን/ሸልፎችን/ እንደሚያካትት የአልማው ተወካይ በዝርዝር ገልጸዋል፡፡

ስንተባበር እንቆማለን፤ሁላችንም በተሰጠን ጸጋ ሁሉ አስተዋጽኦ ብናደርግ ህዝባችንን ለማሻገር ትልቅ አቅም ይኖረናል!
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ሚያዚያ 17/2012ዓ.ም



