የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የጎንደር ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተናበው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ዩኒቨርሲቲው የኮረና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ከማድነቅም ባሻገር በሀገር ውስጥና በሀገር ውጪ የሚገኙ ሀገር ወዳድ ግለሰቦችንና ባለሀብቶችን ለዚሁ ተግባር እንዲተባበሩ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ስለሆነም ከሀገር ውጪ (ከዱባይ ሀገር) ከሚገኙ የጎንደር ከተማና አካባቢ ተወላጆች የተላኩትን 8 የሙቀት መለኪያዎች፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተ/ከንቲባ ኢ/ር ማስተዋል ስዩም ከተረከቡ በኋላ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን እና ለዩኒቨርሲቲው ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ ለዶ/ር አሸናፊ ታዘበው አስረክበዋል፡፡

በተመሳሳይ የአይኔ ሪል ስቴት ባለቤት ወ/ሮ ያይንአበባ ቸሩ ባለ እንድ ፎቅ ዘመናዊ ማረፊያ ቤታቸውን ወቅቱ እስኪያልፍ የኮሮና ቫይረስ/ኮቪድ-19ን ለመመርመር ደፋ ቀና ለሚሉ ሃኪሞች እንዲኖሩበት ፈቅደዋል፡፡ ቤቱን ኢ/ር ማስተዋል፣ ዶ/ር አስራትና ዶ/ር አሸናፊ ቦታው ድረስ በመሄድ ጎብኝተዋል፡፡

ከንቲባው ስለ ተደረገው ሰናይ ተግባር ልባው ምስጋና በማቅረብ፣ ተመሳሳይ እርዳታዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቃል እንደ ተገባላቸውና እንቅስቃሴዎችም እንደተጀመሩ አያይዘው ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብሮ ለማስራት ያለውን ተነሳሽነት በተደጋጋሚ በተግባር ማሳየቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በሽታውን ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር እያደረገው ያለውን ድጋፍና እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ዶ/ር አስራት አድንቀዋል፤ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ አብሮ በመቆም ይኸን አስከፊ ወቅት መሻገር ይገባል::” በማለት የተለመደ መልዕክታቸውንም አያይዘው አስተላልፈዋል፡፡



